ከ11 ቀናት በኋላ በሚካሄደው የቡድን 20 ጉባኤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ይሳተፋሉ
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ህንድ በምታስተናግደው የቡድን 20 አባል ሀገራት ጉባኤ እንደማይሳተፉ ገለጹ።
ፕሬዝዳንቱ ከህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር በስልክ ሲወያዩ በጉባኤው እንደማይሳተፉ ማረጋገጣቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
የሩሲያ መንግስት ቃል አቀባይ ባለፈው ሳምንት ፑቲን “በስራ ጫና” ምክንያት ወደ ህንድ እንደማያመሩ መግለጹ ይታወሳል።
ከፈረንጆቹ መስከረም 9 እስከ 10 2023 በኒው ደልሂ በሚካሄደው ጉባኤ ሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ሰርጌ ላቭሮቭ ትልካለች።
19 የበለጸጉ ሀገራት እና የአውሮፓ ህብረትን ያካተተው የቡድን 20 በኒው ደልሂው ጉባኤ ሩሲያ በዩክሬን ላይ በከፈተችው ጦርነት ላይ ትኩረት አድርጎ ይመክራል ተብሏል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ስናክን ጨምሮ የአባል ሀገራቱ መሪዎች በጉባኤው እንደሚሳተፉ ተገልጿል።
ባለፈው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የብሪክስ ጉባኤ በአካል ያልታደሙት ፑቲን በዚህ ጉባኤ ለመሳተፍ ያልፈለጉበት ትክክለኛ ምክንያት ግልጽ አለመሆኑን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንቱ በጆሃንስበርጉ ጉባኤ በበይነ መረብ ለመሳተፍ የተገደዱት የአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ባወጣባቸው የእስር ማዘዣ ምክንያት ነው።
የቡድን 20 አባል ሀገሯ ህንድ ግን የአይሲሲ ፈራሚ ሀገር ባለመሆኑ ወደ ኒውደልሂ የማያመሩት ከእስር መዛዣው ጋር በተገናኘ አይሆንም።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ባለፈው አመት በኢንዶኔዥያ በተካሄደው የቡድን 20 አባል ሀገራት ጉባኤም አለመሳተፋቸው ይታወሳል።