የጋቦን ወታደሮች ስልጣን ተቆጣጥረናል አሉ
ወታደራዊ አመራሮቹ ስልጣን መያዛቸውን ያሳወቁት የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት አሊ ቦንጎ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን መመረጣቸውን ባሳወቀ በደቂቃዎች ልዩነት ነው
ከ2020 ወዲህ በምዕራብና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራት 8 የመንግስት ግልበጣዎች ተካሂደዋል
የጋቦን ወታደሮች ዛሬ ማለዳ የመንግስት ስልጣን መቆጣጠራቸውን አስታወቁ።
ወታደራዊ አመራሮቹ በሀገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥን (ጋቦን 24) ቀርበው ስልጣን ይዘናል ያሉት የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት አሊ ቦንጎ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን መመረጣቸውን ባሳወቀ በደቂቃዎች ልዩነት ነው።
ወታደሮቹ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ውጤት መሰረዙን እና ሁሉም የሀገሪቱ ድንበሮች መዘጋታቸውንም ነው በመግለጫቸው ያነሱት።
ከወታደራዊ የመንግስት ግልበጣ መግለጫው በኋላ በማዕከላዊ አፍሪካዊቷ ሀገር መዲና ሊበርቪል የተኩስ ድምጽ እየተሰማ መሆኑን ሬውተርስ ዘግቧል።
የሀገሪቱ መንግስት፣ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት፣ ህገመንግስታዊ ፍርድ ቤት እና ምርጫ ኮሚሽኑ መፍረሱንም በጋራ መግለጫቸው ተጠቅሷል።
ወታደራዊ አመራሮቹ “የሽግግር እና የተቋማት መልሶ ግንባታ” የሚል ስያሜ ያለው ኮሚቴ ማዋቀራቸውንም ነው ያስታወቁት።
ከፕሬዝዳንት አሊ ቦንጎ መንግስት እስካሁን የተሰጠ ምላሽ የለም፤ ፕሬዝዳንቱ በምን ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙም እስካሁን አልታወቀም።
የዛሬው የጋቦን መፈንቅለ መንግስት የሚሳካ ከሆነ ከ2020 ወዲህ በምዕራብ እና መካካከለኛው አፍሪካ ስምንተኛው የመንግስት ግልበጣ ይሆናል።
በማሊ፣ ጊኒ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ቻድ እና ኒጀር ባለፉት አመታት ተደጋጋሚ የመንግስት ግልበጣዎች ተደርገዋል።
በካካዋ ምርቷ በምትታወቀው ጋቦን ባለፈው ቅዳሜ የተደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የፕሬዝዳንት አሊ ቦንጎን ቤተሰብ የ56 አመት የስልጣን ጉዞ የሚያስቀጥል መሆኑም አመጽ እንዳይቀሰቅስ ተሰግቶ ነበር።
የ64 አመቱ አሊ ቦንጎ በፈረንጆቹ 2009 ከአባታቸው ኦማር የፕሬዝዳንትነት መንበሩን የተረከቡ ሲሆን የባለፈው ሳምንቱን ምርጫ 64 ነጥብ 27 መራጭ በማግኘት ማሸነፋቸው ተገልጿል።
ምርጫውን አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን እንዳይሰጡት ማድረጋቸውና የታዛቢዎችን ቁጥር መቀነሳቸውም በምርጫው ተአማኒነት ላይ ጥላ አጥልቶበታል ተብሏል።