የታገቱ ተማሪዎች እንዲለቀቁ የሚያሳስቡ ሰልፎች በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ተካሄዱ
በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ሰልፎች ተካሄዱ
በባህርዳር፣በደብረማርቆስ፣በደብረብርሃን፣በሸዋሮቢት፣በፍኖተ ሰላም፣በቆቦ፣በዳንግላ፣በዱርቤቴ፣በአዲስ ቅዳም እና በሌሎቹም የክልሉ ከተሞች የታገቱ ሴት የደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንዲለቀቁ የሚያጠይቁ ባነሮችን የያዙ ሰልፈኞች ወደ አደባባዮች ወጥተዋል፡፡
ዩኒቨርስቲዎች የእውቀት መገብያ እንጂ መሰቃያ ሊሆኑ አይገባም የሚሉ መልዕክቶችን የያዙት ሰልፈኞቹ እገታውን ያወገዙ ሲሆን መንግስት እና መሪዎቹ የተማሪዎቹን ደህንነት ለመጠበቅና ከታገቱ በኋላም ለማስለቀቅ ያሳዩትን ቸልተኝነት ኮንነው፤ በቶሎ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡
ብሄርና ኃይማኖትን መሰረት አድርገው የሚደርሱ ጥቃቶችን መንግስት እንዲያስቆም እና ጥፋተኞች በህግ እንዲጠየቁም ነው ያሳሰቡት፡፡
ብልጽግናን የተቀላቀለው የክልሉ መሪ ፓርቲ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) እና አመራሮቹም በየሰልፎቹ ክፉኛ ተተችተዋል፡፡ የወከሉትን ህዝብ ደህንነትና ጥቅም በማስጠበቅ ረገድ ክፍተት እንዳለባቸው ከማሳየትም በላይ ሃገራዊ ለውጡን ተከትሎ ለህዝቡ ቃል በገቡት ልክ ሆነው አለመገኘታቸውም ተንጸባርቋል፡፡
ሰልፎቹ በየከተሞቹ በሚገኙ የአማራ ወጣት ማህበራት አስተባባሪነት የተዘጋጁ መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡
አ.ብ.መ.ድ እንደዘገበው ከሆነም ሰልፎቹ በተለያዩ የውጭ ሃገራት ተካሂደዋል፡፡