“ዴንሱክ” የተባለው የጃፓን ሐብሐብ በአማካኝ በ188 እና 283 ዶላር ነበር የሚሸጠው
በጃፓን ብቻ የሚገኘውና “ዴንሱክ” የተባለው ሐብሐብ በዓለማችን ላይ ውድ በተባለ ገንዘብ መሸጡ በርካቶችን እያነጋገረ ይገኛል።
“ዴንሱክ” የተባለው የጃፓን ሐብሐብ አንዱ ፍሬ በአማካኝ በ188 እና 283 የአሜሪካ ዶላር ይሸጥ እንደነበረ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
አሁን ላይ ግን “ዴንሱክ” በ6 ሺህ የአሜሪካ ዶላር መሸጡ በርካቶችን አስገርሟል።
በዐይነቱ ልዩ ነው የሚባልለት ይህ የጃፓን ሐብሐብ በሰሜናዊው የሃዲኮ ደሴት ላይ የሚበቅል ሲሆን፤ ባለው የተለየ ጣፋጭነት ከሌሎች የሐብሐብ ዝርያዎች እንደሚለይ ይነገራል።
ሐብሐቡ ጠቆር ያለ ቀይ ቀለም ያለው ሲሆን፤ በውስጡ የሚይዛቸው ፍሬዎችም ከሌሎች የሐብሐብ ዝርያዎች ያነሱ መሆናቸው ይነገራል።
ዴንሱክ ሐብሐብ ከሌሎች የሐብሐብ ዝርያዎች የሚለየው፤ ባለው ጠንካራ እና ጠቆር ያለ ቀይ ቀለሙ እንደሆነም ዘ ጋርዲያንን ጨምሮ ሌሎች ተነባቢ ጋዜጦች አስነብበዋል።
የዚህ አይነት የሀብሐብ ምርት በአፈር ውስጥ በፍጥነት በአግድም እንዲስፋፋ ሰፊ መሬት የሚፈልግ ሲሆን ምርቱ ግን ብዙውን ጊዜ መጠነኛ ነው። በዚህም ከፍተኛ ትኩረት እና እንክብካቤ ይጠይቃል።
“ዴንሱክ” የተባለው የጃፓን ሐብሐብ ከዚህ ቀደም በጃፓን ውስጥ ብቻ የሚለማ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ላይ ግን በአውሮፓ ሀገራት ጭምር ዝርያው መሠራጨቱና ለሽያጭ መቅረቡ ተሰምቷል።