የፍቅር አጋሩን ከአደጋ ለመታገድ 6 ሺህ ኪሎ ሜትሮችን የተጓዘው ጣልያናዊ
ረዘም ለሉ ጊዜያት በቃል ኪዳን ፍቅር የቆዩት ዲፔትሮ እና የናታሊያ በነገው ዕለት ጋብቻቸውን ይፈፅማሉ
በርካቶች ዲፔትሮን ከ“አሳ አጥማጅነት’’ ወደ ‘’ነፍስ አዳኝነት’’ ተቀየረ የፍቅር ሰው ሲሉ እያሞካሹት ነው
የሰው ልጆች በህይወት ዘመናቸው ለሚወዷቸው ሰዎች ሲሉ አስከ ህይወታቸውን እስከማጣት የሚደርስ መስዋእትነት ሲከፍሉ ማየትና መስማት የተለመደ ነው።
የ48 ዓመቱ ጣልያናዊው ዴቪድ ዲፔትሮ ለፍቅር አጋሩ ሲል የሰራው ገድል የበርካታ መገናኛ ብዙሃን ርዕስ ሆኖ ብቅ ብለዋል።
ነገሩ እንዲህ ነው፤ “ብርቱውና ተጽኖ ፈጣሪው የሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቱን የሀገሬ ቀጣይ እጣ ፈንታ አሳስቦኛል እናም በዩክሬን እና ምዕራባውያን መካከል እየተስተወለ ያለው ቅጥ ያጣ ፍቅር ከወዲሁ መልክ ላስየዘው” በሚል፤ በዩክሬን ላይ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመራቸውን ይፋ አደረጉ።
በዚህም የሩሲያ እርመጃ የፈጠረውን አደጋና ሰብዓዊ ቀውስ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዋና አጀንዳ ወደ መሆን ተሸጋገረ።
የዩክሬን ጉዳይ እጅጉን ካስጨነቃቸው ሰዎች አንዱ ጣልያናዊው ዴቪድ ዲፔትሮ ነበር፤ ለምን ቢባል የሚወዳት የፍቅር አጋሩ የሩሲያ የጥይት ቀለሃዎችዎች እና ቦምቦች በሚዘንቡባት የዩክሬኗ መዲና ኪቭ ውስጥ ነበረችና።
በጦርነቱ የተጨነቀው ዲፔትሮ ወደ ዩክሬን በማቅናት የፍቅረኛውን ህይወት ማዳን እንዳለበት ለመወሰን ሁለት ጊዜ እንኳን አላሰበም።
የጣሊያኑ “ላ ሪፐብሊካ ጋዜጣ” እንዳስነበበው ከሆነ፤ ዴቪድ ዲፔትሮ ከሚኖርባት የጣሊያኗ ሲሲሊ ከተማ የጭነት መኪና በመጠቀም ከስራ ባልደረባው ጋር ለሶስት ቀን ከግማሽ ያለ ምንም እረፍት ግማሽ አውሮፓን በሚባል መልኩ ጣልያንን፣ ኦስትሪያን፣ ቼክ ሪፐብሊክን እና ፖላንድን አቋርጦ እስከ ዩክሬን ድንበር ድረስ ተጉዟል።
የዴቪድ ዲፔትሮ የፍቅር አጋር የሆነችው የፊዚዮቴራፒ ባለሙያ ናታሊ በዩክሬን ዋና ከተማ ኪቭ ከሁለት ልጆቿ ጋር ስትኖር የነበረ ሲሆን፤ የቦንብ ጥቃት በኬቭ እንደተጀመረ ናታሊና 2 ልጆቿ በፖላንድ ድንበር ወደሚገኘው የዘመዶቻቸው ቤት ተጠልለው ነበር።
ነገር ግን ሁኔታው እምብዛም አስተማማኝ ስላልነበረ ዲፔትሮ በህይወቱ ላይ ከባድ ውሳኔ በመወሰን የህይወት አጋሩን ለማዳን ተጓዘ።
ዲፔትሮ በፌስቡክ ገጹ ላይ በሰፈራቸው ቪድዮዎች እና ፎቶዎች ናታሊን ለማዳን እና አብራው እንድትኖር ለማድረግ ከጣልያን ወደ ዩክሬን ሊወስዳት የሄደበትን ዝርዝር ሁኔታን ለታዳሚያን አጋርቷል።
ከየካቲት 28- መጋቢት 3 ያለምንም እንቅልፍ ለሶስት ቀን ከግማሽ ከጓደኛው ጋር በመሆን የተጓዘው ዲፔትሮ በመጨረሻም ፍቅረኛውን እና ሁለት ልጆቹን አግኝቶ ከቤተሰቡ ጋር ወደ ሲሲሊ ተመልሷል።
አሁን ላይ ዲፔትሮ ለፍቅር አጋሩ ሲል የከፈለው መስዋእትነት በራካቶችን እያነጋገረ ነው።
በርካቶች የዲፔትሮ ድርጊት ‘’ፍቅር’’ ከሁሉም ነገር የሚበልጥ፣ጠንካራ ድንበር እና ወሰን የማይገድበው መሆኑ ትልቅ ማሳያ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።
ከአሳ አጥማጅነት’’ የሚተዳደረው ጣልያናዊ ወደ ‘’ነፍስ አዳኝነት’’ ተቀየረ የፍቅር ሰው በማለት ዲፔትሮን የሚያሞካሽ ርዕስ ይዘው የወጡ የጣልያን ጋዜጦችም ጥቂት አይደሉም።
ዲፔትሮ እና የናታሊያ ረዘም ላሉ ጊዜያት በቃልኪዳን የቆዩ ሲሆን፤ በነበራቸው እቅድ መሰረት በነገው ዕለት መጋቢት 11 ጋብቻ የሚፈጽሙ ይሆናል።
በዩክሬን የተፈጠረው ትርምስ በከባድ መስዋእትነት የታጀበውን የጥንዶቹ የፍቅር ታረክ ውብ እንደሚያደረግውም በርካቶች በመግለጽ ላይ ናቸው።