የቀድሞው የአፍጋኒስታን የፋይናንስ ሚኒስትር በአሜሪካ የታክሲ ሹፌር መሆናቸው እያነጋገረ ነው
ካሊድ ፓዬንዳ እንዲህ ዐይነት እጣ ፋንታ የገጠማቸው የመጀመሪያው የአፍጋኒስታን ሚኒስትር አይደሉም
ከወራት በፊት ቢሊዮን ዶላሮችን ያንቀሳቅሱ የነበሩት ካሊድ ፓዬንዳ ታሊባን አፍጋኒስታንን እስከተቆጣጠረበት ጊዜ ድረስ ሃገራቸውን በፋይናንስ ሚኒስትርነት አገልግለዋል
የቀድሞው የአፍጋኒስታን የፋይናንስ ሚኒስትር በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ የኡበር ታክሲ ሹፌር መሆናቸው እያነጋገረ ነው፡፡
ከወራት በፊት 6 ቢሊዮን ዶላር ይጠጋ የነበረውን የአፍጋኒስታንን አመታዊ በጀት ያንቀሳቅሱ የነበሩት ካሊድ ፓዬንዳ አሁን የራይድ ሹፌር ናቸው፡፡ ይህም ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል፡፡
የ40 ዓመቱ ካሊድ ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ዓመት 2021 ወርሃ ጥር ላይ ነበር በቀድሞው የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት አሽራፍ ጋኒ ተሾመው ሃገራቸውን በፋይናንስ ሚኒስትርነት ማገልገል የጀመሩት፡፡
ታሊባን አፍጋኒስታንን እስከተቆጣጠረበት እስካሳለፍነው ወርሃ ነሐሴ መጨረሻ ድረስ ለ8 ወራት ያህል ሃገራቸውን በፋይናንስ ሚኒስትርነት አገልግለዋል፡፡
ሆኖም ታሊባን የፕሬዝዳንት አሽራፍ ጋኒን መንግስት ገርስሶ ስልጣን መቆጣጠሩን ተከትሎ ካሊድ ቤተሰባቸውን ይዘው ወደ አሜሪካ ለመሰደድ ተገደዋል፡፡
በአሜሪካ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በትርፍ ሰዓት የተለያዩ ኮርሶችን በማስተማር እና የተለያዩ ንግግሮችን በማድረግ ኑሯቸውን ይመሩ ነበር፡፡ ኤሊኖይን ጨምሮ በጆርጅ ታውን ዩኒቨርስቲም በተጋባዥ እንግድነት አስተምረዋል፡፡
ሆኖም ይህ ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር አልበቃም፡፡ በመሆኑም የአራት ልጆች አባት የሆኑት የ40 ዓመቱ ካሊድ በኡበር ታክሲ ሹፍርና መስራትን መርጠዋል፡፡
ይህ በመሆኑ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ አመስጋኝ መሆናቸውን ለዋሽንግተን ፖስት የተናገሩት የቀድሞው የአፍጋኒስታን ሚኒስትር የብቸኝነትና ባዶ የመሆን ስሜት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል፡፡
ከወራት በፊት ቢሊዮን ዶላሮችን ያንቀሳቅሱ የነበሩት ሚኒስትር ዛሬ ከጉዞ ደንበኞቻቸው ዳረጎት የሚጠብቁ የታክሲ ሹፌር ሆነዋል፡፡
በ‘ቲፕ’ መልክ ከደንበኞቻቸው ከሚያገኙት ገንዘብ በተጨማሪ ኡበር በ2 ቀናት ውስጥ 50 ደንበኞችን የሚያገለግሉ ከሆነ 95 ዶላር በጉርሻ መልክ እንደሚሰጣቸውም ገልጸዋል፡፡
ካሊድ ፓዬንዳ እንዲህ ዐይነት እጣ ፋንታ የገጠማቸው የመጀመሪያው የአፍጋኒስታን ሚኒስትር አይደሉም፡፡ ወደ ጀርመን የተሰደዱት የአፍጋኒስታን የቀድሞ የኮሙንኬሽን ሚኒስትር ሰይድ ሳዳት በእቃ አመላላሽነት ተቀጥረው መስራት ጀምረዋል መባሉ ይታወሳል፡፡