ስምምነቱ የተቋረጠው “ብዙ ፈተናዎች” በተባለ ምክንያት መሆኑ ተገልጿል
በ300 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ሊገነቡ የነበሩት የጋድና የዲቼቶ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ስምምነት መቋረጡን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢትዮጵያ መንግስት እና የሳዑዲ አረቢያው “ኤሲደብሊውኤ ፓወር” የተሰኘው ኩባንያ፣የጋድና የዲቼቶ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ቢስማሙም ፕሮጀክቶቹ ሳይገነቡ ስምምነቱ መፍረሱ ይፋ ሆኗል።
አል ዐይን አማርኛ ከሚኒስቴሩ ባገኘው መረጃ መሰረት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶቹን ለመገንባት ተፈርሞ የነበረው ስምምነት በሁለቱም ወገኖች ፈቃድ እንዲቋረጥ ተደርጓል። ስምምነቱ የተቋረጠበት ምክንያት በዝርዝር ባይገለጽም “በብዙ ፈተናዎች” ምክንያት የሚል ጉዳይ ተጠቅሷል።
ስምምነቱ መቋረጡን ተከትሎ በሚኒስቴሩ የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት ዳይሬክቶሬት ሌላ ጨረታ እንደሚያወጣም ነው የተገለጸው።
በአውሮፓውያኑ 2019 ይፋ ከተደረጉ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች መካከል የሆኑት ሁለቱ ፕሮጀክቶች፣ እያንዳንዳቸው 150 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጾ ነበር።
እነዚህ ፕሮጀክቶች በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት ለመሥራት የታቀዱ ሲሆን፤ በድምሩ 250 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት ይኖራቸዋል ተብሎ ነበር።
“ኤሲደብሊውኤ ፓወር” የተሰኘው ኩባንያ፣ ለ20 ዓመታት የኃይል ሽያጭ ለማከናወን በአንድ ኪሎ ዋት በሰዓት 2 ነጥብ 5260 ዶላር ለማስከፈል ተስማምቶ ነበርም ተብሏል።