ኢትዮጵያ፤ሱዳን ያለባትን ውዝፍ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ እንድትከፍል ጠየቀች
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሱዳን የ“እንከፍከላለን” ምላሽ ሰጥታለች ብሏል
ሱዳን ከአምስት እስከ ስድስት ወር የሚሆን የኤሌክትሪክ ክፍያ አለመክፈሏን የኢትዮጵያ መንግስት ገልጿል
ኢትዮጵያ፤ ሱዳን ያልከፈለቻትን ውዝፍ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ እንድትከፍላት መጠየቋን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልገለጸ፡፡
እስካሁን ሱዳን ከአምስት እስከ ስድስት ወራት የሚሆን የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያ አለመክፈሏንም ተቋሙ ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የ2014 ዓ.ም ስድስት ወራት አፈጻጸሙን ለገንዘብ ሚኒስቴር ባስገመገመበት ወቅት፤ሱዳን ውስጥ ባለው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት ሀገሪቱ ለኢትዮጵያ መክፈል የነበረባትን የስድስት ወራት ክፍያ መፈጸም አለመቻሏን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሞገስ መኮንን ለአል ዐይን አማርኛ እንደገለጹት ሱዳን ያልከፈለችው የኤሌክትሪክ ክፍያ መኖሩን ገልጸው፤ ይህ ግን ከዚህ ቀደምም የሚያጋጥም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በፊትም ሱዳን የተጠቀመችውን የኤሌክትሪክ ውዝፍ ክፍያ ትከፍል እንደነበር የገለጹት አቶ ሞገስ የአሁኑም ከቀደመው ጊዜ የተለየ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተገኘው መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ ለሱዳንና ጂቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረበች ነው፡፡
ሁለቱም ሀገራት ውዝፍ ክፍያ ቢኖርባቸውም ቀደም ሲል ባለው አሰራር መሰረት ውዝፍ ክፍያውን እንደሚከፍሉ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያም፤ ሱዳን ለተጠቀመችው ኤሌክትሪክ የሚጠበቅባትን ክፍያ እንድትከፍል መጠየቋን አቶ ሞገስ የገለጹ ሲሆን፤ ሱዳኖችም ክፍያውን እንደሚከፍሉ እንጠብቃለን ብለዋል፡፡
ሱዳን ክፍያውን እንድትፈጽም ከኢትዮጵያ ለቀረበላት ጥያቄም የ “እንከፍከላለን” ምላሽ ሰጥታለች ተብሏል፡፡
ሱዳን የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያውን ባለመፈጸሟ ኃይል እንደማይቋረጥ የገለጹት አቶ ሞገስ ይሄ አዲስ ነገር እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ፤ ሱዳን የተጠቀመችበትን ክፍያ ከመክፈልም ባለፈ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመግዛት ጥያቄ ማቅረቧንም ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡ እስካሁን ለሱዳን እና ጅቡቲ 100 ሜጋ ዋት ኃይል እየተሸጠ መሆኑ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ በቀጣይ ግን ይህ ቁጥር ከሀገር ውስጥ አቅርቦት ሁኔታ ጋር እየታየ ሊጨምር እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ሱዳን ፤ 1200 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ከኢትዮጵያ ለመግዛት ጥያቄ ማቅረቧ የተገለጸ ሲሆን ይህም በኢትዮጵያ በኩል እየታየ ነው ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ጎረቤቶች የኃይል አቅርቦት ጥያቄ እያቀረቡላት ሲሆን ሶማሊላንድ እና ደቡብ ሱዳን ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡