ኢትዮጵያ 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለደቡብ ሱዳን ልትሸጥ ነው
ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችላትን የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራርማለች
በኃይል ሽያጭ ሥምምነቱ በመጀመሪያ ዙር 100 ሜጋ ዋት ኃይል ለደቡብ ሱዳን ይቀርባል
ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን በኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር መፍጠር የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የፈረሙት በኢትዮጵያ በኩል በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሱልጣን ወሊ ሲሆኑ፤ በደቡብ ሱዳን በኩል በኢነርጂና ግድብ ሚኒስትርቶም ረሚስ ጆን ናቸው።
በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ ለደቡብ ስዳን በአጠቃላይ 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የምታቀርብ መሆኑም ተመላክቷል።
በስምምነቱ በመጀመሪያ ዙር 100 ሜጋ ዋት ኃይል ሲሆን በሂደት ደግሞ መሰረተ ልማትን በማጠናከር የሽያጭ መጠኑን በየደረጃው ወደ 400 ሜጋ ዋት ለማሳደግ ነው ተብሏል።
የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮቹም ሁለት ምዕራፎች ያሉት ሲሆን የመጀመሪያው ከጋምቤላ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ እስከ ደቡብ ሱዳኗ መልካን ከተማ 357 ኪሎ ሜትር የ250 ኪሎ-ቮልት መስመር ዝርጋታን ያካተተ ነው።
ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ከ400 እስከ 500 ኪሎ-ቮልት ተሸካሚ መስመሮችን ኤሳ ቴፒ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ እስከ ደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ የሚዘረጋ 700 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ነው ተብሏል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን በስፋት ከታዳሽ የኢነርጂ ምንጮች ከውሃ፣ከእንፋሎትና ከንፋስ ኃይል ለማመንጨት በስፋት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን መካከል የተፈረመው ስምምነት በሁለቱ እህትማማች ሀገራት መካከል ድንበር ተሻጋሪ የኃይል ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል የኃይል መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለማከናወን የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል።
የደቡብ ሱዳን የኢነርጂና ግድብ ሚኒስትር ፒተር ማርሴሎ ናስር በበኩላቸው በደቡብ ሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል የኃይል ትስስር መፍጠር የዜጎች ሕይወት ለማሻሻል የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
የኃይል ትስስሩ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት እንደሚያጠናክርም መናገራቸውንም ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ እስካሁን ለሱዳንና ለጅቡቲ ኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ እያገኘች መሆኑ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ፤ ሱዳን ያልከፈለቻትን ውዝፍ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ እንድትከፍላት መጠየቋ የሚታወስ ሲሆን፤ ሱዳን ከአምስት እስከ ስድስት ወራት የሚሆን የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያ አለመክፈሏን ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መግለጹ ይታወሳል።