በአዲስ አበባ ስርዓተ ቀብር ለመፈጸም እስከ 20 ሺህ ብር እንደሚጠየቅ ያውቃሉ?
የተወሰኑት ቤተ ዕምነቶች የአገልግሎት ክፍያ ጭማሪ ሊያደርጉ መሆኑን ገልጸዋል
አዲስ አበባ ከ85 በላይ ስርዓተ ቀብር መፈጸሚያ ቦታዎች አሏት
በአዲስ አበባ ስርዓተ ቀብር ለመፈጸም ከ460 ብር እስከ 20 ሺህ ብር እንደሚጠየቅ ያውቃሉ ?
ከዚህ ውስጥ 15ቱ የመንግስት ሲሆኑ ከ70 በላይ የሚሆኑት ደግሞ በተለያዩ ቤተ ዕምነቶች ባለቤትነት ስር የሚገኙ መሆናቸውን አል ዐይን አማርኛ የአዲስ አበባ ዘላቂ ማረፊያ እና መናፈሻ ኤጀንሲ ያገኘው መረጃ ያስረዳል።
እንደ ኤጀንሲው መረጃ ከሆነ በመንግስት ባለቤትነት ሰር ካሉ 15 ዘላቂ ማረፊያዎች ወይም ስርዓተ ቀበር መፈጸሚያ ስፍራዎች መካከል 13ቱ አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው።
በቦሌ ቡልቡላ እና በጀሞ አካባቢ ያሉ ሁለት ዘላቂ ማረፊያዎች ከወሰን ማስከበር ጋር የተያያዙ ስራዎች ባለመጠናቀቃቸው አገልግሎት እየሰጡ አይደለም።
አል ዐይን አማርኛ በከተማዋ ባሉ ዘላቂ ማረፊያዎች የስርዓተ ቀበር አገልግሎት ምን እንደሚመስል ተዘዋውሮ ምልከታ አደርጓል።
በጉለሌ ክፍለ ከተማ ስር የሚገኘው የቀጨኔ መድሀኒዓለም ዘላቂ ማረፊያ ከተመለከተው ስርዓተ ቀብር መፈጸሚያ ስፍራዎች መካከል አንዱ ነው።
ይህ ዘላቂ ማረፊያ ከ1962 ዓ.ም ጀምሮ የቀብር አገልግሎት በመስጠት ላይ ሲሆን 11 ሺህ 179 ካሬ ሜትር ስፋት አለው።
በዚህ ስፍራ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተከርስቲያን ዕምነት ተከታዮች እና ባይተዋሮች ማለትም ወዳጅ ዘመድ የሌላቸው ሰዎች ስርዓተ ቀብራቸው በዚህ ስፍራ ይፈጸማል።
መሬቱ የመንግስት በመሆኑ ስርዓተ ቀብር ሲፈጸም የመሬት ከፍያ በነጻ ሲሆን የአገልግሎት ከፍያ ለመንግስት 100 ብር ብቻ መክፈል ግዴታ ነው።
ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ቀብር አስፈጻሚ ተብለው ለተደራጁ ማህበራት የቀብር ቦታን ለማስዋብ፣ ሀውልት ለማሰራት እና ሌሎች አገልግሎቶችን ለማግኘት ከ460 ብር ጀምሮ እስከ 7 ሺህ 400 ብር ድረስ እንደሚያስከፍል አል ዐይን አማርኛ በምልከታው እንዲሁም ከዘላቂ ማረፊያው እና ቀብር ከሚያስፈጽሙ የሟች ቤተሰቦች አረጋግጧል።
በዚህ ስፍራ የተቀበረ አስከሬን ለ7 ዓመታት ከቆየ በኋላ ተነስቶ ወደ ሌላ ማጠራቀሚያ ስፍራ ይወሰዳል፤ መሬቱም ለሌላ ስርዓተ ቀብር መፈጸሚያ ይዘጋጃል።
አል ዐይን በከተማዋ ተዘዋውሮ በተመለከታቸው ሌሎች የተለያዩ ቤተ ዕምነቶች ለሰባት ዓመት ለሚቆይ አስከሬን የስርዓተ ቀብር መፈጸሚያ ስፍራዎች በአንድ ሰው ከ20 ሺህ ብር በላይ እንደሚያስከፍሉ ከቤተ ዕምነቶቹ ለማረጋገጥ ችሏል።
የተወሰኑት ቤተ ዕምነቶች ከዚህም በላይ ለማስከፈል እና የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ በጥናት ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በነዚህ ቤተ ዕምነቶች የሟች ቤተሰቦች አስከሬናቸውን ለ7 ዓመት ካቆዩ በኋላ በዚያው እንዲቀጥል ከፈለጉ ክፍያ እንደ አዲስ እንደሚጠይቁም ከነዚሁ ቤተ ዕምነቶች ሰምተናል።