ኢትዮጵያ ከ2014 ዓ/ም ጀምሮ ሰላምን በዩኒቨርስቲዎች ደረጃ ልታስተምር ነው
በ2014 ዓ.ም በሁለተኛ ወሰነተ ትምህርት ላይ መሰጠት እንደሚጀምርም ነው የተገለጸው
ትምህርቱ በሙከራ ደረጃ በተመረጡ ስድስት ዩኒቨርሲቲዎች የሰላም ትምህርት መሰጠት ይጀምራል ተብሏል
በ2014 ዓ.ም በተመረጡ ስድስት ዩኒቨርሲቲዎች በሙከራ ደረጃ የሰላም ትምህርት መሰጠት ሊጀመር መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ጋር በመተባበር በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሰላም ትምህርት ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆኑ ተገልጿል።
ሚኒስቴሩ ከዩኔስኮ እና ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከተውጣጡ ምሁራን ጋር በጉዳዩ ላይ በቢሾፍቱ ከተማ ምክክር እያደረገ ነው።
በምክክሩም በተመረጡ ስድስት ዩኒቨርሲቲዎች በሙከራ ደረጃ የሰላም ትምህርት የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል እንደ ኢዜአ ዘገባ።
ጎንደር፣ ዋቸሞ፣ አሶሳ፣ ሰመራ፣ ቡሌ ሆራ እና ደንቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲዎች የመጀመሪያ የሙከራ ትግበራ የሚደረግባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው።
በ2014 ዓ.ም በሁለተኛው ወሰነተ ትምህርት (ሴሚስተር) ላይ ትምህርቱን መሰጠት ይጀመራል ተብሏል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ የሰላም ትምህርት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መስጠት ያስፈለገው ነባራዊ አገራዊ ሁኔታውን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው ብለዋል።
በዚህም ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚስተዋሉ የሰላም እጦት ችግሮችን ለመፍታት ትምህርቱ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።
ከሙከራው የሚገኙ ልምድና ተሞክሮዎችን በመቀመር በመላ አገሪቱ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርቱን የመስጠት እቅድ እንዳለም አንስተዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በዚሁ ዙሪያ ከዩኔስኮ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑም ተገልጿል።