“የተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች የኢትዮጵያን የአጎዋ አባልነት ቢያጠናክሩ እንጂ ሌላ የሚያሳስቡ አይደሉም”- የጠ/ሚ ዐቢይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪ
አንዳንድ ሎቢ ተቋማት ‘መንግስት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እየፈጸመ ነው’ በሚል ማግባቢያ ኢትዮጵያ ከአጎዋ እንድትወጣ ግፊት በማድረግ ላይ ይገኛሉ
“የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹ ካልቆሙ በወደፊት የኢትዮጵያ የአጎዋ አባልነት ጉዳይላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ”-የአሜሪካ የንግድ ተወካይ
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት አማካሪ እና የኢትዮጵያ ዋና የንግድ ተደራዳሪ ማሞ ምህረቱ እስመለዓለም ባለፉት ሶስት ዓመታት የተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች የኢትዮጵያን የአጎዋ አባልነት ቢያጠናክሩ እንጂ ሌላ የሚያሳስቡ አይደሉም ሲሉ አስታወቁ፡፡
ከፍተኛ አማካሪው ከአሜሪካ የንግድ ተወካይ አምባሳደር ካትሪን ታይ ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታዎች እና በአጎዋ አባልነቷ ጉዳይ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ አሜሪካ እና ኢትዮጵያ ታሪካዊ ምጣኔ ሃብታዊ እና ተጨማሪ አብሮ የማደግ አቅም አላቸው ያሉት አምባሳደር ካትሪን ዓለም አቀፋዊ እውቅና ያላቸው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ካልቆሙ የኢትዮጵያን የወደፊት በአጎዋ አባልነት ጉዳይ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ በሚል ለከፍተኛ አማካሪው አቶ ማሞ መናገራቸውን አስታውቀዋል፡፡
“ግልጽ እና ገንቢ” ላሉት ውይይት ያመሰገኑት አቶ ማሞ በበኩላቸው አሜሪካ እና ኢትዮጵያ ጠንካራ ምጣኔ ሃብታዊ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
አጎዋ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የስራ ዕድሎችን የፈጠሩ አምራች ተቋማት የሚደገፉበት መንገድ እንደሆነም ነው ያብራሩት ፤ 80 በመቶ ያህሉ የስራ ዕድሎች በሴቶች መያዛቸውን በመጠቆም፡፡
አቶ ማሞ መንግስት ባለፉት ሶስት ዓመታት ለኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍን የሚከፍቱ ዘርፈ ብዙ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ የለውጥ እርምጃዎችን ወስዷልም ነው ያሉት እነዚህ እርምጃዎች የኢትዮጵያን የአጎዋ አባልነት ቢያጠናክሩ እንጂ ሌላ የሚያሳስቡ እንዳይደሉ በመጠቆም፡፡
ከፍተኛ አማካሪው የበለጠ መቀራረብን ተስፋ እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል፡፡
አጎዋ (AGOA) የአፍሪካ አገራት ምርታቸውን ከቀረጥና ኮታ ነፃ ወደ አሜሪካ ገበያ እንዲያስገቡ የሚረዳው ስምምነት ነው፡፡
ሆኖም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ልታደርግ ከምትፈልግባቸው የግንኙነት ዘርፎች መካከል አንዱ እየሆነ መምጣቱን የሚናገሩ በዝተዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት በፈረጀው ህወሓት እና መንግስትን በሚቃወሙ አንዳንድ አካላት ተቀጥረዋል የሚባሉ አንዳንድ አግባቢ (ሎቢ) ተቋማት “መንግስት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እየፈጸመ ነው” በሚል ማግባቢያ ኢትዮጵያ ከአጎዋ ስምምነት እንድትወጣ ግፊት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
ለዚህም ቮን ባተን-ሞንታግ-ዮርክ (Von Batten-Montague-York) ተጠቃሽ ነው፡፡