በኢትዮጵያ ሁለት ሚሊዮን ዜጎች ለጎርፍ ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገለጸ
የአፋር እና የሶማሌ ክልል መንግስታት ለአደጋ ጊዜው የሚሆኑ ጀልባዎችን አዘጋጅተዋልም ተብሏል
ለአደጋው ሊጋለጡ የሚችሉ ዜጎችን ለመደገፍ አራት ቢሊዮን ብር ገደማ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል
በክረምት ወራት በሚከሰት ዝናብ ሁለት ሚሊዮን ዜጎች ለጎርፍ አደጋ ሊጋለጡ እንደሚችሉ ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኮሚሽኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ በ 10 ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል መረጃ መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡ በተሰበሰበው መረጃ መሰረትም ሁለት ሚሊዮን ዜጎች ለጎርፍ አደጋ ሊጋለጡ እንደሚችሉ ነው ዳይሬክተሩ ያስታወቁት፡፡
እስካሁን በተጠናቀረው መረጃ መሰረት ለጎርፍ ሊጋለጡ ይችላሉ የተባሉት 56 ዞኖች እና 244 ወረዳዎች እንደሆኑም ነው አቶ ደበበ ያነሱት፡፡
አቶ ደበበ እንደገለጹት በአፋር ክልል አሳዒታ፣ ዱለቻ እና ገዋኔ ወረዳዎች የጎርፍ አደጋ ሊከሰትባቸው የሚችሉ ቦታዎች ናቸው፡፡
ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የአየር ሁኔታ መረጃውን ከብሔራዊ ሜቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ ጋር በማግኘት የቅድመ ማስጠንቀቂያ፤ የምላሽ እና መልሶ ማቋቋም ስራ እየሰራ እንደሆነም ተነስቷል፡፡
ኤጀንሲው በበኩሉ በቀጣዮቹ 10 ቀናት በሚኖር ከባድ ዝናብ ቅጽበታዊ ጎርፍ እና ሌሎች አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ አሳስቦ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሜቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ የአየር ሁኔታ እና የአየር ጸባይ ትንበያ ባለሙያ አቶ ታምሩ ከበደ በቀጣዮቹ 10 ቀናት በሚኖር ከባድ ዝናብ ቅጽበታዊ ጎርፍ እና ሌሎች አደጋዎች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ለአል ዐይን አማርኛ የተናገሩ ሲሆን ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንም በዚህ መረጃ መሰረት ስራዎቹን እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የተፋሰስ ባለሥልጣን ጎርፍ ሊከሰትባቸው ይችላሉ ባላቸው ቦታዎች ላይ በ700 ሚሊዮን ብር ማፋሰሻ ቦዮች (ዳይክ) መስራቱንም የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ለጎርፍ አደጋ ይጋለጣሉ ተብለው ለሚጠበቁት ዜጎች ከመንግስት፣ ከአጋር ድርጅቶች እና ከማህበረሰቡ የሚውጣጣ ሶስት ቢሊዮን 957 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ አቶ ደበበ ተናግረዋል፡፡
የክልል መንግስታት የጎርፍ አደጋውን ለመከላከል በራሳቸው በጀት መመደባቸው የተገለጸ ሲሆን አፋር ክልል አራት ሶማሌ ክልል ደግሞ አምስት ጀልባዎችን ማዘጋጀታቸው ተገልጿል፡፡
ከሰሞኑ በአፋር ክልል አውሲ-ረሱ ዞን አሳዒታ ወረዳ አዋሽ ወንዝ ከመጠን በላይ በመሙላቱ ምክንያት በሦስት ቀበሌዎች ላይ የጎርፍ አደጋ መከሰቱ የሚታወስ ነው፡፡
የክልሉ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሀፈት ቤት በአደጋው አንድ መቶ አባዎራዎች መፈናቀላቸውንና በ 50 ሄክታር የእርሻ መሬት ላይ ጉዳት መድረሱን መግለጻቸውም አይዘነጋም፡፡
በባለፈው ዓመት ክረምት በአፋር ክልል ከ 31 ሺ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውንና 200 ሺ ሰዎች ንብረታቸው መውደሙን ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ስራ አመራር ኮሚሽን መግለጹም ይታወሳል፡፡