ሰላይ ናቸው የተባሉት ፊኛዎች ጉዳይ የአሜሪካ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ፍጥጫን እያባባሰ ነው ተባለ
ቤጂንግ፤ ቻይና አሜሪካ በአየር ክልሌ ላይ ፊኛዎች አብራለች ስትል ወቅሳለች
ቻይና ፤በአሜሪካ ሰማይ ላይ ታይተዋል ስለተባሉት “ሰላይ ፊኛዎች” የማውቀው ነገር የለም ማለቷ አይዘነጋም
ሰላይ ናቸው የተባሉትን የፊኛዎች ጉዳይ የአሜሪካ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ፍጥጫ እያባባሰ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ከሰሞኑ አሜሪካ የቻይና የስለላ ፊኛ ነው ያለችውን ፊኛ በጥይት መትቻለሁ ማላቷ እንዲሁም ቻይና አሜሪካ በአየር ክልሌ ላይ ፊኛዎች አብራለች በማለት በሁለቱም ኃያላን ሀገራት መካከል ያለውን ፍጥጫ ይበልጥ አክሮታል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትእዛዝ ካስተላለፉ በኋላ በአሜሪካ እና በካናዳ ድንበር ላይ ባለ የአየር ክልል ላይ የነበረውን ፊኛ ተመትቶ መውደቁ ፔንታጎን ከቀናት በፊት ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
“በርካታ የስለላ ሴንሰሮች” የተገጠሙለትና 60 ሜትር ያህል ቁመት ያለው ፊኛን አትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ለመጣል ኤፍ-16 ተዋጊ ጄት ጥቅም ላይ መዋሏንም ጭምር ነበር የተገጸው፡፡
በተጨማሪም የአሜሪካ ጦር በራዳር ውስጥ ያልገቡትን ሌሎች ፊኛዎች ለምምታት ሶስት ጥይቶች መተኮሱን ፔንታጎን አስታውቋል፡፡
ዋሽንግተን ይህን ትበል እንጅ ቻይና ፤ በአሜሪካ ሰማይ ላይ ታይተዋል ስለተባሉት “ሰላይ ፊኛዎች” የምታውቀው ነገር እንደሌለ መግለጿ ይታወሳል፡፡
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “ቤጂንግ ስለእነዚያ በአሜሪካ እና ካናዳ ተመትተው ወደቁ ስለተባሉት ፊኛዎች ምንም አይነት መረጃ የላትም” ነበር ያለው ሰኞ እለት ባወጣው መግለጫ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዋይት ሀውስ ማክሰኞ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ፊኛዎች የቻይና የስለላ መርሃ-ግብር አካል ስለመሆኑ የሚጠቁም ነገር አልተገኘም ማለቱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ያም ሆኖ አሁን በፊኛው ጉዳይ የተፈጠረው አጀንዳ በሁለቱም ሀገራት መካከል የነገሰውን ውጥረት በቀላሉ ሊያረግበው እንዳማይችል ይነገራል፡፡
በተለይም አየር ክልሏን የመጠበቅ አቅሟ ልል መሆኑ ለተጋለጠችው አሜሪካ ፤ ግንኙነትን ወደ ተለመደው ዲፕልማሲያዊ ንግግር ለመመለስ ሊያስቸግራት ይችላል ተብሏል፡፡
የቅርቡ የአሜሪካው ከፍተኛ ዲፕሎማት አንቶኒ ብሊንከን የቤጂንግ ጉብኝት ማራዘምም የዚሁ አንዱ አካል እንደሆነ ይነሳል ፡፡