በአሜሪካ ሰማይ የታዩት ፊኛዎች “በአንዳች ሃይል የተገፉ” ናቸው - ቻይና
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፥ የአሜሪካ ፖለቲከኞችና ሚዲያዎች ቻይናን ያለወንጀሏ ማብጠልጠላቸውን ተቃውሟል
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፥ ከቻይና ባለስልጣናት ጋር በስልክ መክረዋል
በአሜሪካ ሰማይ ላይ የታዩት ሁለት የቻይና ፊኛዎች ጉዳይ አሁንም መነጋገሪያነቱን ቀጥሏል።
አንደኛው ፊኛ ወደ መካከለኛው የአሜሪካ ክፍል ፤ ሁለተኛው ደግሞ ወደ ላቲን አሜሪካ እየተጓዙ መሆኑን የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ገልጿል።
ፊኛዎቹ የአሜሪካን የአየር ክልል ጥሰው ገብተው እየሰለሉ ነው የሚል ወቀሳውም ተበራክቷል።
ቻይና ግን በዛሬው እለት ባወጣችው መግለጫ ወቀሳውን አስተባብላለች።
ክስተቱ “በአንዳች ሃይል የተፈጠረ ተአምር” እንጂ ሆን ተብሎ የተፈጸመ እንዳልሆነም ነው የገለጸችው።
ቤጂንግ ቀደም ብላም ፊኛዎቹን አቅጣጫ ያስቀየረው ያልተጠበቀ ንፋስ መሆኑን መግለጿን ሬውተርስ ዘግቧል።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፥ የአሜሪካ ባለስልጣናት እና የመገናኛ ብዙሃን አጋጣሚውን ቻይናን ለማብጠልጠል መጠቀማቸውን ተቃውሟል።
“ቻይና ሁሌም ለአለም አቀፍ ህግ መከበር ቁርጠኛ ናት፤የሀገራትን ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነትም ታከበራለች” ነው ያለው መግለጫው።
የፊኛዎቹ በአሜሪካ ሰማይ ላይ መታየት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በቻይና ከነገ ጀምሮ ሊያደርጉት የነበረውን ጉብኝት እንዲያራዝሙ አስገድዷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ፥ “የቤጂንግ ድርጊት ተቀባይነት የሌለውና ሃላፊነት የጎደለው” ነው ብለዋል።
ብሊንከን ከጉዟቸው ባሰናከላቸው ጉዳይ ከቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ የውጭ ጉዳዮች ኮሚሽን ዳይሬክተሩ ዋንግ ይ ጋር ትናንት ምሽት መምከራቸው ተገልጿል።
ዋንግ በዚሁ ወቅት ሁለቱም ሀገራት ከመካሰስ ይልቅ በሰከነ መንገድ መነጋገር እንዳለባቸው ለብሊንከን ነግረዋቸዋል ይላል የሬውተርስ ዘገባ።
ብሊንከን በበኩላቸው “ፊኛዎቹ ከአየር ክልላችን ማስቀጣቱን ቅድሚያ እንሰጠዋለን፤ ሁኔታዎች ሲፈቅዱም ቻይናን የምጎበኝ ይሆናል” ማለታቸው ተጠቁሟል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከነገ ጀምሮ በቤጂንግ ጉብኝት ሊያደርጉት የነበረው ጉብኝጥ ከሶስት አመት በላይ የሻከረውን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ያድሳል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።