ውይይቱ ፎርቲስኪው በተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት እና በውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር መካከል የተካሄደ ነው
በኢትዮጵያ ተጨማሪ 25 ጂጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል ውይይት ተካሄደ
ተጨማሪ 25 ጂጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል ውይይት ዛሬ በሸራተን አዲስ ሆቴል መካሄዱን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ውይይቱ ፎርቲስኪው ከተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር የተካሄደ ነው፡፡
15ቱን ጂጋ ዋት ከውሃ 10 ጂጋ ዋት ደግሞ ከጂኦ ተርማል ለማመንጨት እንደሚፈልግ ያስታወቀው ድርጅቱ 10 ቢሊዮን ዶላር ፈሰስ ማድረግ እንደሚፈልግም በውይይት መድረኩ አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ ይዞት የመጣው እድል ለኢትዮጵያ ትልቅ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ መንግስት የኃይል ተደራሽነትን ለማስፋት የግል ባለሃብቱን ባሳተፈ መልኩ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
አሁን ያለውን 45 በመቶ የኃይል ተደራሽነት እኤአ በ2030 መቶ በመቶ ለማድረስ ታቅዷል ያሉም ሲሆን ኢትዮጵያ አሁን ለጎረቤት ሃገራት እያቀረበች ያለውን 350 ሜጋ ዋት ኃይል በጥቂት ዓመታት ውስጥ ወደ 700 ሜጋ ዋት ለማሳደግ እንደምትሰራ ነው የገለጹት፡፡
ለዚህ የሚሆኑ ምቹ እና ሰፊ አማራጮች እንዳሏትም ገልጸዋል፡፡
በአውስትራሊያ በጊኒና በሌሎችም ሃገራት ውጤታማ ስራ መሥራቱን በውይይቱ የገለጸው ድርጅቱ በበኩሉ በኢትዮጵያ የኃይል ልማት ዘርፍ የመሰማራት ከፍ ያለ ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል፡፡
ፎርቲስኪው በማዕድን ፣ በማዳበሪያ፣ በኃይል ማመንጨት፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና በሌሎችም ሥራዎች ላይ የተሰማራ ዓለም አቀፍ የግል ንግድ ድርጅት ነው፡፡