ኢትዮጵያ የታጁራ ወደብን ለመጠቀም የሚያስችላትን መንገድ ገንብታ አጠናቀቀች
በሲሚንቶ ኮንክሪት የተገነባው 78 ኪሎ ሜትሩ መንገድ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጥቶበታል
መንገዱ ወደ አሰብ ወደብ የሚዘልቀው መንገድ አካል ጭምርም ሲሆን በጅቡቲ ወደብ ያለውን ጫና ያቀላል ተብሏል
ኢትዮጵያ የታጁራ ወደብን ለመጠቀም የሚያስችላትን የመንገድ ፕሮጀክት ገንብታ አጠናቀቀች
ኢትዮጵያ አዲሱን የታጁራ ወደብ ለመጠቀም የሚያስችላትን የመንገድ ፕሮጀክት በአፋር ክልል ገንብታ ማጠናቀቋን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
መንገዱ ከዲቾቶ ተነስቶ በጋላፊ መገንጠያ/ዶቢ-ኤሊዳር በኩል ወደ በልሆ የሚዘልቅ ነው ያለው ባለስልጣኑ 78 ኪ.ሜ ርዝመት ኖሮት በሲሚንቶ ኮንክሪት መገንባቱን ገልጿል፡፡
2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የወጣበት መንገዱ በመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ የተገነባ ነው ፡፡
ወጪው በመንግስት የተሸፈነ ሲሆን በገጠር ግራና ቀኝ ትከሻውን ጨምሮ 10 ሜትር በከተማ (ኤሊዳር) አካባቢ ደግሞ 21.5 ሜትር ስፋት እንዲኖረው ሆኖ ተገንብቷል፡፡
በሲሚንቶ ኮንክሪት መገንባቱ የአካባቢውን ሞቃታማ የአየር ንብረት ተቋቁሞ ረዥም አመታትን ለማገልገል እንዲችል በማሰብ ነው፡፡
በአነስተኛ ጥገና እስከ 40 አመት ድረስ ሊያገለግል ይችላልም ተብሏል፡፡
መንገዱ ወደ አዲሱ የታጁራ ወደብ መዳረሻ ብቻም ሳይሆን ወደ አሰብ ወደብ የሚዘልቀው የመንገድ አካል ጭምርም ነው።
መገንባቱም በጅቡቲ ወደብ ይፈጠር የነበረውን የትራንስፖርት ጫና ከማቅለል ባሻገር በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ የፖታሽ ክምችትም ሆነ ሌሎች ማዕድናትን በቀላሉ ወደ ወደብ ለማድረስ ያስችላል፡፡