የህወሓት ትጥቅ መፍታት እና ከመከላከያ ውጭ ያሉ ኃይሎች ከትግራይ መውጣት በአንድ ጊዜ እንዲከውን ስምምነት ላይ ተደርሷል
በናይሮቢ የተፈረመው የሰላም ስምምነቱ ማስፈፀሚያ እቅድ ህወሃት ትጥቅ የሚፈታበትን ሂደት አመላክቷል
የሰብአዊ ድጋፍ ያለምንም ገደብ እንዲደርስም የፌደራሉ መንግስት ሃላፊነቶችን ዘርዝሯል
የፌደራል መንግስቱ እና ህወሓት በዛሬው እለት በኬንያ ለፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት ማስፈጸሚያ የሚሆን እቅድ ተፈራርመዋል፡፡
እቅዱ ህወሓት በተስማማው መሰረት ትጥቅ የሚፈታበትን ዝርዝር ሁኔታ አካቷል፡፡
የፌደራል መንግስት እና የህወሃት ወታደራዊ አዛዦች፥ ከመጪው ረቡዕ ጀምሮ ባሉት ሰባት ቀናት ውስጥ ለወታደሮቻቸው ማብራሪያ እንዲሰጡ ይደረጋል ይላል የሰላም ስምምነቱ ማስፈፀሚያ ሰነድ።
ከማብራሪያው በኋላ ባሉት አራት ቀናትም የህወሃት ሃይሎች ያሉበትን ቦታ ለቀው የፌደራሉ መንግስት ይቆጣጠረዋል ነው የሚለው ሰነዱ።
ከዚህም በመቀጠል የፌደራል መንግስቱ ባለስልጣናት ሃላፊነት ተረክበው በትግራይ የተቋረጡ አገልግሎቶችን ወደማስጀመር እንደሚገቡ ስምምነት ይጠቅሳል፡፡
የከባድ መሳርያዎች ትጥቅ አፈታትን በተመለከተ በሰፈረው አንቀጽ፣ የህወሓት ከባድ መሳሪያ ትጥቅ መፍታት እና የውጭ ኃይሎች እና ከመከላከያ ውጭ ያሉ ኃይሎች ከትግራይ መውጣት በአንድ ጊዜ እንዲከውን ስምምነት ተደርሷል ይላል።
በሌላ በኩል የቀላል መሳሪዎዎች ትጥቅ አፈታትን በተመለከተ በ14 ቀናት ውስጥ ግልፅ ማስፈፀሚያ ሰነድን የሚያዘጋጅ የጋራ ኮሚቴ እንዲቋቋም ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በናይሮቢ የተፈረመው የሰላም ስምምነቱ ማስፈፀሚያ ሰነድ በአንቀፅ 3 የንፁሃንን ደህንነት የተመለከቱ ነጥቦች ሰፍረዋል። በአንቀፅ 4 ደግሞ ያልተገደበ የሰብአዊ ድጋፍን ወደ ትግራይ ለማድረስ የፌደራሉ መንግስት ሃላፊነት ተዘርዝረዋል።