የፌደራል መንግስት እና ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ማስፈጸሚያ እቅድ ተፈራረሙ
የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስትና የህወሓት ወታደራዊ አመራሮች በኬንያ ሲወያዩ ቆይተዋል
የፌደራል መንግስት እና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ በዘላቂነት ግጭት ለማቆም መስማማታቸው ይታወሳል
የፌደራል መንግስት እና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተስማሙትን ዘላቂ ተኩስ አቁም ስምምነት ለማስፈጸም የሚያችል ስነድ ላይ በኬንያ ተፈራርመዋል፡፡
“የፕሪቶሪው ስምምነት ማስፈጸሚያ ሰነድ ተፈርሟል፡፡ ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለው መርህ በድጋሚ ሰርቷል” ሲሉ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከፊርማ ስነ ስርአቱ በኋላ በትዊተር ገጻቸው ጸፈዋል፡፡
የፌደራል መንግስቱና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ በደረሱት ስምምነት መሠረት በኬንያ የሁለቱ አካላት ወታደራዊ አመራሮች ሲመክሩ ቆይተዋል።
የስምምነቱን ማስፈጸሚያ እቅድ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና በህወሓት በኩል ጀነራል ታደሰ ወረደ ተፈራርመዋል፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ወታደራዊ አዛዦች ያደረጉት ንግግረ ዘላቂ ሰላምን የሚያመጣ ነው ብለዋል።
ላለፉት ስድስት ቀናት በናይሮቢ የተደረገው ወታደራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ምክክር በሁለቱም ወገን በጥሩ መንፈስ መካሄዱንም ነው ያነሱት።
መንግስት በፕሪቶሪያ ለተደረሰው የሰላም ስምምነትም ሆነ ዛሬ ለተፈረመው የስምምነቱ ማስፈፀሚያ እቅድ ድንጋጌ ተፈፃሚነት ቁርጠኛ መሆኑንም አብራርተዋል።
ጀነራል ታደሰ ወረደ በበኩላቸው የተደረሰው ስምምነት በትግራይ የሚታየውን የህዝብ ሰቆቃ የሚያስቆም ነው ብለዋል።
ጦርነቱን ማስቆም ብቻ ሳይሆን የሰብአዊ ድጋፎችን ለማድረስ እና የተቋረጡ አገልግሎቶችን ለማስጀመር በናይሮቢ የተፈረመው ሰነድ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጄነራሉ ተናግረዋል፡፡
በደቡብ አፍሪካው ስምምነት ህወሐት ትጥቅ እንዲፈታ፣ በትግራይ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲመለሱ እና የፌደራል መንግስቱ በትግራይ ያሉ የፈረደራል ተቋማትን እንዲቆጣጠር ሁለቱ አካላት መስማማታቸው ይታወሳል።