የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና የህወሓት ወታደራዊ አመራሮች በኬንያ ሊገናኙ ነው ተባለ
በደቡብ አፍሪካ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለመተግበር እነቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል
የህወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ በሚፈቱበት ሁኔታ የሁለቱ ወታደራዊ አመራሮች በስልክ መነጋገራቸውን አምባሳደር ሬድዋን አስታወቁ
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና የህወሓት ታጣቂዎች ወታደራዊ አመራሮች የፊታችን ሰኞ በኬንያ ናይሮቢ እንደሚገናኙ ተገለጸ።
በደቡብ አፍሪካዋ ፕሪቶሪያ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን አስታወቁ።
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የስምምነት ሂደቱን አስመልክቶ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ሲካሄድ የነበረው የድርድር ውጤት በሳለፍነው ረቡዕ ምሽት ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
በድርድሩ ስምምነት ከተደረሰባቸው ጉዳዮች ውስጥም ግጭትን በዘላቂነት ማቆም፣ ሰብዓዊ እርዳታን ያለገደብ ማድረስ፣ በሀገሪቱ ህገ መንግስት መሰረት ህግና ስርዓትን ማስከበር አንዲሁም የህወሓት ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታትየሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ማብራሪያቸው በስምምነቱ መሠረት የህወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ በሚፈቱበት ሁኔታ ላይ ለመወያየት የሁለቱ ወታደራዊ አመራሮች የስልክ ልውውጥ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በዚህም የሁለቱ ወታደራዊ አመራሮች የፊታችን ሰኞ በኬንያ ናይሮቢ እንደሚገናኙ እና ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ውይይት እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል።
ጥቅምት 24፤2013 ዓ.ም ሁለተኛ ዓመቱን የደፈነው የሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት በተለይም በጦርነት ቀጠናው ባሉ ክልሎች ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት አስከትሏል።
ይህንን ጦርነት አስቁሞ ሰላም እንደሚያመጣ ተስፋ የተጣለበት የሰላም ድርድር ባሳለፍነው ረቡዕ በደቡብ አፈሪካዋ ፕሪቶሪያ መፈረሙ ይታወሳል።
በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን እና በህወሓት በኩል ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ 10 ገፆችና 15 አንቀፆች ባሉት የሰላም ስምምነት ሰነድ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡
የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ የተደረሰው ስምምነት ትልቅ ብስራት ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም ባሳለፍነው ሃሙስ በአርባ ምንጭ ከተማ ባደረጉት ንግግር ላይበድርድሩ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት ያነሳቸው ሁሉም ሀሳቦች ተቀባይነት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
መንግስት ለስምምነቱ ተግባራዊነት ቁርጠኛ መሆኑን እና በትግራይ መልሶ ግንባታ እንደሚካሄድም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።