በቀይ ባህር በንግድ መርከቦች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እየተስፋፋ እንደሚገኝ ተነገረ
ማርስክ የተባለው የኮንቴነር ጫኝ ድርጅት በአካባቢው ያለው የደህነነት ስጋት እስከ 20 በመቶ ድረስ የስራ አቅሙን እንደቀነስው አስታውቋል
በኢራን የሚደገፉት የየመን ሀውቲ ታጣቂዎች በቀጠናው የደቀኑት ስጋት በአጠቃላይ የአለም ንግድ ስርአት ላይ እክል ፈጥሯል፡
በቀይ ባህር በንግድ መርከቦች ላይ በተደጋጋሚ የሚያጋጥመው መስተጓጎል እየተበራከተ እንደመጣ ማርስክ አስታወቀ፡፡
የዴንማርኩ ግዙፍ የባህር ሎጂስቲክ አገልግሎት አፍሪካ ፣ እስያ እና አውሮፓ በዚህ ችግር ምክንያት እየተፈተኑ እንደሚገኙ ድርጅቱ ተናግሯል፡፡
በእስራኤል እና ሀማስ መካከል ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ከአሜሪካ እና እስራኤል ጋር ግንኙነት ባላቸው የንግድ መርከቦች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን የፈጸሙት ሀውቲዎች፤ እስራኤል ከጋዛ እስከምትወጣ ድረስ ጥቃት ማድረሳቸውን እንደሚቀጥሉ መዛታቸውን ተከትሎ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የንግድ መርቦች የደህንነት ስጋት አጥልቶባቸዋል፡፡
በቀጠናው ለደህነነት አስተማማኝ ሁኔታ ባለመኖሩ አማራጭ መተላለፊያዎችን ለመጠቀም ተገደናል ያለው ማርስክ ይህም ውጭዎችን እንዲጨምር በማድረጉ በሸቀጦች ዋጋ ላይ ንረት እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑን ነው ያነሳው፡፡
ቀደም ባለው ጊዜ ወደ አውሮፓ በሚያሻግረው ስዊዝ ቦይ እና ወደ ባብ ኤል መንደብ መተላለፊያ ለመድረስ በሚደረገው ጉዞ ላይ ስጋቶች የነበሩ ሲሆን አሁን ላይ ወደ ሩቅ ምስራቅ እና እስያ መተላለፊያዎች ላይ ተመሳሳይ እክሎች እንደሚያጋጥሙት ነው የመርከብ ድርጅቱ ያስታወቀው፡፡
በዚህ የተነሳም የመርከቦቹን የመጫን አቅመ ከ15 እስከ 20 በመቶ እንዲቀንስ በማድረግ የሀውቲዎችን ጥቃት ሽሽት ተጨማሪ ጊዜ እና ወጪ በሚጠይቀው አፍሪካን ኬፕ በተባለ መተላለፍያ በመጠቀም ላይ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡
ወደ መካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ ዋነኛ የምርት ምንጭ እንደሆነ በሚነገርለት እስያ እየተስፋፋ የመጣው የደህንነት ስጋት በቀጣይ በንግድ ስርአቱ ላይ ከፍተኛ ችግር ከማስከተሉ በፊት መፍትሄ እንዲበጅለት መጠየቁን ሮይተርስ አስነብቧል፡፡
የአለም 30 በመቶ የንግድ ኮንቴነሮች በሚተላለፉበት ቀይ ባህር ካሳለፍነው መጋቢት ወር ጀምሮ በባብ ኤል መንደብ እና በስዊዝ ካናል የሚተላለፉ መርከቦች በግማሽ ቀንስዋል፡፡
በነዚህ ሁለት መተላለፍያዎች በአመት ከ30ሺ - 50 ሺ መርከቦች ይተላለፋሉ፤ 12 በመቶ የአለም ንግድ ፣ 15 በመቶ የአለም ነዳጅ ምርት ፣ የእስያ እና አውሮፓ 40 በመቶ ንግድ በነዚህ መስመሮች የሚተላለፍ ነው፡፡
በአጠቃላይ ሁለቱ አህጉሮች ብቻ እስከ 700 ቢሊየን ዶላር ድረስ የሚወጣ የንግድ ሸቀጦቻቸውን ስጋት ላይ በወደቀው መስመር ያሳልፋሉ፡፡
በአጠቃላይ በቀይ ባህር 1.8 ትሪሊየን የሚያወጣ ሸቀጥ የሚተላለፍ ሲሆን ይህ መጠን እስከ 2050 ድረስ 6.1 ትሪሊየን ዶላር እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡