14 አሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ለመመለስ ፈቃደኛ ሲሆኑ አብዛኛው ጅቡቲ ቀርተዋል
የትራንስ ኢትዮጵያ አዲስ ተወካይ ከጅቡቲ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በጅቡቲ ቆመው የነበሩና የኩባንያው ንብረት የሆኑ 179 ከባድ ተሽከርካሪዎችን ቁልፎች ከትናንት በስቲያ ሰኞ ጥር 03 ቀን 2013 ዓ.ም ተረክበዋል።
ተሽከርካሪዎቹ ሕወሓት በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ጥቃት ከመፈፀሙ ጥቂት ቀናት በፊት የቀድሞ የትራንስ ኢትዮጵያ አመራሮች ከጅቡቲ ወደብ እቃዎችን ለማምጣት በሚል ወደ ጅቡቲ ወስደው እንዲቆሙ ያደረጓቸው ናቸው፡፡
በጅቡቲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባደረገው ጥረት አሁን ላይ ተሽከርካሪዎቹ ወደ ሀገር እንዲመለሱ ለማድረግ የቁልፍ ርክክብ መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
አዲሱ የትራንስ ኢትዮጵያ ኩባንያ ተወካይ ከጅቡቲ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የኩባንያው ንብረት የሆኑ 179 ከባድ ተሽከርካሪዎችን ቁልፎች ተረክበዋል።
የኢትዮጵያ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትራንስ ኢትዮጵያ በወንጀል የሚፈለጉትን የሕወሓት መሪዎች በገንዘብ በመደገፍ፣ በህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ በመሳሪያ የታገዘ ዘረፋ እና ሌሎች ወንጀሎች በመጠርጠር ተሸከርካሪዎቹ እንዲመለሱ ትዕዛዝ ሰጥቶ እንደነበር ተገልጿል።
ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ፈቃደኛ ከሆኑት 14 አሽከርካሪዎች በስተቀር ቀሪዎቹ በጅቡቲ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ እንደሚገኙም ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡