ጅቡቲ የሚገኙ የትራንስ ኢትዮጵያ ከባባድ ተሽከርካሪዎችን ለማስመለስ እየተሰራ ነው ተባለ
የህወሓት አባል እና የቀድሞ ታጋይ የነበሩ አሽከርካሪዎች ተሽከርካሪዎቹን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ፈቃደኛ ባለመሆን ተልዕኮው እንዳይሳካ ጥረት ሲያደርጉ ነበር ብሏል ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ
ተሽከርካሪዎቹ እስከሚመለሱ ድረስ ጠንካራ ጥበቃ እየተደረገላቸው እንደሚገኝም ተገልጿል
ንብረትነታቸው የትራንስ ኢትዮጵያ የሆኑ እና ጅቡቲ የሚገኙ 179 የደረቅ እና 4 የፈሳሽ ጭነት ማጓጓዣ ከባባድ ተሽከርካሪዎችን ለማስመለስ እየሰራ እንደሆነ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታወቀ፡፡
በጉዳዩ ላይ ጅቡቲ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር እየተሰራ ነው ያለው ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ከጅቡቲ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የዐቃቤ ህግ እና የፖሊስ ተቋማት የበላይ አመራሮች ጋር የተሳካ ውይይት መደረጉን አስታውቋል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉት የጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ በወንጀል የተገኙ ሀብቶች ማስመለስ ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ዓለምአንተ አግደው ተሽከርካሪዎቹ እስከሚመለሱ ድረስ በኢትዮጵያ እና በጂቡቲ መንግስታት ትብብር ጠንካራ ጥበቃ እየተደረገላቸው ይገኛል ብለዋል፡፡
የህወሓት አባል እና የቀድሞ ታጋይ የነበሩ አሽከርካሪዎች ተሽከርካሪዎቹን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ፈቃደኛ ባለመሆን ተልዕኮው እንዳይሳካ ጥረት ሲያደርጉ ነበር ብሏል ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ፡፡
ሆኖም ተሽከርካሪዎቹን ለመመለስ ተገቢውን ጥረት ማድረጉን እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡
ትራንስ ኢትዮጵያ በተለያዩ የወንጀል ተግባር ውስጥ ተሳትፈዋል በሚል ተጠርጥረው ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የንብረት እገዳ ከጣለባቸው የትዕምት (ኢፈርት) ድርጅቶች መካከል አንዱ መሆኑ ይታወሳል፡፡