ፖለቲካ
ከምርጫ ክልል ጋር በተያያዘ በተነሳ ተቃውሞ ተዘግቶ የነበረው የኢትዮ- ጅቡቲ መንገድ ተከፈተ
መንገዱ አሁን ተከፍቶ መደበኛ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ተጀምሯል ተብሏል
መንገዱ “የምርጫ ክልላችን ባልተገባ መንገድ ተካለለ” በሚሉ የአፋር ወጣቶች ተዘግቶ ነበር
ገዳማይቱ ተብሎ በሚጠራው የአፋር እና የሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ ላይ ተዘግቶ የነበረው የኢትዮ-ጅቡቲ መንገድ መከፈቱን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
ዛሬ ረፋድ “የምርጫ ክልላችን አፋር ክልል መሆን እያለበት ወደ ሶማሊ ክልል ባልተገባ መንገድ ተካለለ” በሚል ቅሬታ ባነሱ የአካባቢው ሰዎች የኢትዮ ጅቡቲ ዋና መንገድ ተዘግቶ ነበር።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ቃል አቀባይ አቶ ጄይላን አብዲ ለአል ዐይን አማርኛ እንዳሉት “ዛሬ ረፋድ አዳይቱ እና ገዳማይቱ በተባሉ አካባቢዎች የኢትዮ ጅቡቲ መንገድ ተዘግቶ የትራንስፖርት እንቅስቃሴው ተስተጓጉሎ ነበር”።
አሁን ላይ ግን “በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና የክልሉ አመራሮች አማካኝነት በተሰራ ስራ ተዘግቶ የነበረው መንገድ ተከፍቶ የትራንስፖርት እንቅስቃሴው ወደ ነበረበት ተመልሷል” እንደ አቶ ጄይላን ገለጻ።
በአካባቢው ከአሁን ቀደምም ህይወት የጠፋባቸው ግጭቶች ጭምር ደጋግመው ማጋጠማቸው የሚታወስ ነው፡፡