ኢትዮጵያ በቶኪዮ ኦሎምፒክ ሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ከገቡ 70 ሀገራት ውስጥ በ55ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች
ከ125 ዓመት በፊት በግሪክ የተጀመረው የኦሎምፒክ ውድድር ዘንድሮ በጃፓን ቶኪዮ እየተካሄደ ነው።
ላለፉት 125 ዓመታት በርካታ የዓለማችን ሀገራት በተሳተፉባቸው የኦሎምፒክ ውድድሮች ሜዳሊያዎችን ያሸነፉ ቢሆንም ከ60 በላይ ሀገራት ደግሞ አንድም ሜዳሊያ አሸንፈው ወደ ሀገራቸው ይዘው እንዳልመጡ ዋሸንግተን ፖስት ዘግቧል።
ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ለ206 የዓለማችን ሀገራት የአባልነት እውቅና ሰጥቶቸው በኦሎምፒክ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
የዘንድሮውን 2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ ውድድርን ሳይጨምር በዓለማችን ካሉ ሀገራት መካከል ከ60 በላይ ሀገራት ሜዳሊያ አሸንፈው አያውቁም።
በየአራት ዓመቱ አንዴ የሚካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር ከተመሰረተበት በፈረንጆቹ 1896 አንስቶ በመጀመሪያው እና በሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች ከተካሄደባቸው ዓመታት ውጪ በሌሎቹ የተሳታፊ ሀገራት ቁጥር ቢለያይም ሲካሄድ ቆይቷል።
ሜዳሊያ ካላሸነፉ ሀገራት መካከል ከአፍሪካ አንጎላ፤ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፤ ቻድ፤ ሶማሊያ፤ ደቡብ ሱዳን፤ ማዳጋስካር ፤ማሊ፤ቡርኪና ፋሶ፤ሩዋንዳ እና ማላዊ ይጠቀሳሉ።
ከእስያ ሀገራት ደግሞ ባንግላዲሽ፤ምንያማር ወይም በርማ እና የመን ሲሆኑ ከአውሮፓ አልባኒያ፤ቦስኒያ እና ሄርዞጎቪኒያ በታሪክ አንድም ጊዜ የኦሎምፒክ ሜዳሊያ ያላሸነፉ አገራት ናቸው።
ከላቲን አሜሪካ ሀገራት ውስጥ ደግሞ ቦሊቪያ በኦሎምፒክ ውድድር ታሪክ ሜዳሊያ ያላገኘች ብቸኛዋ አገር እንደሆነች ተጠቅሷል።
የ2020 ቶኪዮ ኦሎምፒክ ውድድርን ሳይጨምር እስካሁን በተከሄዱ የኦሎምፒክ ውድድሮች አሜሪካ 2 ሺህ 827 ሜዳሊያዎች ዩናየትድ ኪንግደም 883 ሜዳሊያዎች፤ ጀርመን 855 ሜዳሊያዎች፤ ፈረንሳይ 840፤ ጣልያን 701 ሜዳልያዎች ስዊድን 652 ሜዳሊያዎች፤ቻይና 608 ሜዳሊያዎች፤ ሩሲያ 546 ሜዳሊያዎች እንዲሁም ኖርዌይ እና ካናዳ 520 እና 501 ሜዳሊያዎችን የሰበሰቡ 10 የዓለማችን ቀዳሚ አገራት ናቸው።
ከአፍሪካ ኬንያ በ103 ሜዳሊያዎች አንደኛ ስትሆን ደቡብ አፍሪካ በ86 ሜዳሊያዎች ሁለተኛ ኢትዮጵያ በ54 ሜዳሊያዎች ሶስተኛ ግብጽ በ32 ሜዳሊያዎች 4ኛ ደረጃን ስትይዝ ናይጀሪያ ደግሞ በ25 ሜዳሊያዎች 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
በጃፓን አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 32ኛው የ2020 የቶክዮ ኦሎምፒክ ከተጀመረ ዛሬ 9ኛ ቀኑን አስቆጥሯል። የቶክዮ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች መጀመሩን ተከትሎም በርካታ ውድድሮች ፍጻሜ እያገኙ ሲሆን፤ በርካታ ሀገራትም የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባት ጀምረዋል።
እስካሁን ሰዓት ድረስ ቻይና የሜዳሊያ ሰንጠረዡን በ23 የወርቅ፣ 14 የብር እና 13 የነሃስ በድምሩ በ50 ሜዳሊያዎች በመምራት ላይ ትገኛለች።
አሜሪካ በ20 የወርቅ፣ 20 የብር እና 21 የነሃስ በድምሩ በ55 ሜዳሊያዎች 2ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ ጃፓን ደግሞ በ17 የወርቅ እና በ5 የብር እና 8 የነሃስ በድምሩ በ30 ሜዳሊያዎች በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
በአፍሪካ ደረጃ ደግሞ ደቡብ አፍሪካ በ1 የወርቅ እና 2 የብር ሜዳሊያዎች ከዓለም 29ኛ ስትሆን ከአፍሪካ ደግሞ 1ኛ ላይ ተቀምጣለች፤ ቱኒዚያ በ1 የወርቅ እና በ1 የብር ከዓለም 42ኛ ከአፍሪካ 2ኛ፤ ኢትዮጵየ ደግሞ በ1 የወርቅ ሜዳሊያ ከዓለም 55ኛ ከአፍሪካ ደግሞ 3ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ዩጋንዳ በአንድ የብር እና በአንድ የነሀስ እንዲሁም ግብጽ በሁለት የነሀስ ሜዳሊያዎች ከአፍሪካ 4ኛ እና አምሰትኛ ደረጃይ ይዘዋል። እስካሁን ባለው መረጃም 70 ሀገራት የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባት መቻላቸውን ከቶኪዮ ኦሎምፒክ ድረገጽ ላይ የገኘነው መረጃ ያስረዳል።