የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት የትግራይ ግጭት የኢትዮጵያን አንድነት ባስጠበቀ መልኩ በውይይት እንዲፈታ ጠየቁ
ፕሬዝዳንት ማክሮን ከጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር በስልክ ተወያይተዋል
ትግራይ ክልል ያለውን ግጭት ለመፍታት ሁሉም አካላት ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲመጡ ፕሬዝዳንት ማክሮን ጠይቀዋል
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በሰሜን ኢትዮጵያ፤ በትግራይ ክልል ያለው ግጭት የኢትዮጵያን አንድነት ባስጠበቀ መልኩ በውይይት እንዲፈታ ጠየቁ።
ፕሬዝዳንት ማክሮን በዛሬው ዕለት ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር በስልክ ተወያይተዋል።
የመሪዎቹ ውይይትም በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ግጭት ዙሪያ መሆኑን አል ዐይን ኒውስ ከኤሊዜ ቤተ መንግሥት ጽህፈት ቤት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ፕሬዝዳንቱ በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ያለውን ግጭት ለመፍታት ሁሉም አካላት ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲመጡም መጠየቃቸውን የፈረንሳይ ቤተ መንግስት ጽ/ቤት በመግለጫው አስታውቋል።
የኢትዮጵያን አንድነት ባስጠበቀ መልኩ በግጭት ላይ እየተሳተፉ ያሉ ኃይሎች በሙሉ ፖለቲካዊ ውይይት ሊያደርጉ እንደሚገባም ፕሬዝዳንት ማክሮን ጥሪ አቅርበዋል ተብሏል።
በትግራይ ክልል ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመፍታት እርዳታዎች በአስቸኳይ እንዲደርሱ የጠየቁት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ዕርዳታ እንዳይደርስ የሚያደርጉ ገደቦችም እንዲነሱ ጠይቀዋል።
ፕሬዝዳንት ማክሮን፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ኃላፊ እና አስቸኳይ ዕርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ገሪፊትስ የሚያደርገውን ጥረት ፓሪስ እንደምትደግፍም አስታውቀዋል።
ከድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች በተጨማሪም ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አስታውቀዋል።