ሰዎች በስትንፋሳቸው መጨረሻ በብዛት የሚጸጸቱባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?
በጠና ታማው ለረጅም ጊዜ በአልጋ ላይ የዋሉ ሰዎችን የሚያስታምሙ ሀኪሞች ከልምዳቸው የሰዎች የጸጸት መነሻ ናቸው ያሏቸውን ጉዳዮች አጋርተዋል
በብዛት የሰዎች ጸጸት ሕይወትን በሚዛን ካለመምራት እንደሚመነጭ ሀኪሞቹ ተናግረዋል
ዘላለማዊ ያልሆነው የሰው ልጅ የምድር ቆይታውን ሲያጠናቅቅ ወደ ማይቀርበት ሞት ማቅናቱ የህይወት ኡደት ነው፡፡
በምድር ላይ በሚኖረው ቆይታም እንደሚያሳልፈው ውጣ ውረድ ፣ እንደሚያድግበት ማህበረሰብ እና በህይወት እንደሚያገኘው ልምድ ማንነቱን ይቀርጻል፡፡
የሚሞትበትን ጊዜ ያማያውቀው የሰው ልጅ በምድር ላይ ማድረግ እና ማሳካት የሚፈልጋቸውን ነገሮች ሲያሳድድ የእድሜው ማምሺያ ላይ ይደርስ ወደ ሞት ይጓዛል፡፡
ታዲያ በዚህ ጊዜ አንዳንዶች በዘመናቸው ይጠቅመኛል ብለው ትኩረት የሰጡት ነገር እንዳሰቡት ሳይሆን ሲቀር አልያም ማድረግ ሲኖርባቸው ባላደረጉት ነገር በመጨረሻው ሰአት ይጸጸታሉ፡፡
ሾሻና አንገርላይደር በጽኑ ታመው ለረጅም ጊዜ በሆስፒታሎች ውስጥ የሚተኙ ተማማሚዎችን የሚያክሙ ዶክተር ናቸው። ዶክተሯ ከሲኤንቢሲ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሰዎች ወደ ሞት በተጠጉ ቁጥር ነገን ማሰብ አቁመው ዛሬ እና ትላንት ብቻ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ ብለዋል፡፡
በዚህ ወቅት በብዛት አምልጦኛል በሚሉት ጊዜ ስላላደረጉት ወይም ስላደረጉት ነገር እያነሱ ጸጸታቸውን ይገልጻሉ፡፡
በእነዚህ ሰዎች ዘንድ ነገ የሚባል ነገር የለም የሚሉት ዶክተር ሾሻና እድል ቢያገኙ ማስተካከል የሚፈልጓቸው ጉዳዮች ብቻ ይበልጥ እንደሚያስጨንቋቸው ይገልጻሉ፡፡
በርካታ ሰዎች በስትንፋሳቸው መጨረሻ በብዛት የሚጸጸቱባቸው ነገሮች በሚል ከዘረዘሯቸው ነጥቦች መካከል ቀዳሚው ከቤተሰብ እና ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር በቂ ጊዜ አለማሳለፍ ነው፡፡
ቅድሚያ የሚያስፈልጋቸው በሚመስሉ ቁሳዊ ነገሮች ላይ በማተኮር ለቤተሰብ ፣ ለሚስት ፣ ለባል ፣ ለልጅ እና ለሌሎችም የቅርብ ሰዎች በቂ ጊዜ አለመሰጠት ሰዎች ከሚጸጸቱባቸው ጉዳዮች መካከል አንደኛው ሆኗል፡፡
ሌላው በስራ ላይ የሚጠፋ ሰፊ ጊዜ ነው። ነገን የተሻለ ለማድረግ እና ሕይወትን ለመመራት ሰዎች በስራቸው ውስጥ ጠልቀው መግባታቸው ህይወት የምታቀርባቸውን ሌሎች ስጦታዎች እንዳይመለከቱ ህይወታቸው በሙሉ ከስራ ጋር ብቻ የተቆራኝ እንዲሆን ያደርጋል፡፡
በዚህም ከሰዎች ጋር ይበልጥ እንዳይገናኙ ፣ በበዓላት እና ማህበረሰባዊ መሰባሶች ላይ እንዳይሳተፉ ፣ ሌሎች ሀገራትን እንዳይጎበኙ እና በጥቅሉ ሕይወትን በቅጡ እንዳያጣጥሙ ከሚያደርጉ ጉዳዮች መካከል በስራ ላይ ከመጠን በላይ ጊዜን ማጥፋት ይጠቀሳል፡፡
ዛሬን አለመኖር የሰዎች የጸጸት ምንጭ ናቸው ተብለው ከተጠቀሱ ነጥቦች መካከል እንዱ ነው፡፡
በእቅድ እና በሃላፊነት መመራት መጪውን ታሳቢ ያደረጉ ውሳኔዎችን ማሳለፍ ተገቢ ቢሆንም ነገ ላይ በማተኮር በእጅ ላይ ያለ ዛሬን ማጣት ደግሞ ለጸጸት ይዳርጋል ነው የተባለው፡፡
ዶክተር ሾሻና ይህ መርህ በ20 ፣ በ50 ፣በ80 እና በየትኛውም እድሜ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ይሰራል ያሉ ሲሆን፤ ገና ባልጨበጥነው የነገ ሁኔታ ላይ ከመጠን በላይ ከመጨናነቅ ይልቅ በእጃችን ላይ በሚገኘው ዛሬ ቁምነገር መስራት እና ደስተኛ ሆነን ማሳለፍ ላይ ማተኮር ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በስተመጨረሻም የሰዎች ጸጸት የሚመነጨው በአንድ ጉዳይ ላይ ትኩረት ስናደርግ ሌላውን በመዘንጋት በጥቅሉ ህይወትን በሚዛን ካለመምራት የሚነሳ በመሆኑ ለሁሉም እንደየመጠኑ አስፈላጊውን ትኩረት እና ጊዜ በመስጠት ከጸጸት የጸዳ ህይወትን ለመምራት ያስችላል ተብሏል፡፡