እስራኤል እያደረሰች በምትገኝው ጥቃት ሊባኖስ በታሪኳ አይታው የማታውቀው ተፈናቃይ ሊያጋጥማት እንደሚችል ተነገረ
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ጥቃቱ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ በሚሊየን የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች እንደሚኖሩ ተናግረዋል
በሌላ በኩል በቅርቡ እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በእግረኛ ጦር ጥቃት ልትከፍት እንደምትችል እየተነገረ ነው
በሊባኖስ እስራኤል እየፈጸመችው በምትገኘው የአየር ጥቃት ንጹሀን ዜጎች በከፍተኛ የደህንነት ስጋት ውስጥ እንደሚገኙ የሊባኖሱ ጠቅላይ ሚንስትር ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር ናጂብ ሚካቲ ወቅታዊ ሁኔታዎችን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ የሁኔታዎች እየተባባሰ መምጣት እንዲሁም የእስራኤል የአየር ጥቃት መጠናከር ሊባኖስ በታሪኳ አይታው የማታውቀው የሰዎች መፈናቀል ሊያስከትልባት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ከዋና ከተማዋ ቤሩት ፣ ከደቡባዊ ድንበር አካባቢዎች እና ከሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የሚፈናቀሉ ዜጎች መጨመራቸውን ነው ያነሱት፡፡
የአካባቢው ባለስልጣናት እና ሆስፒታሎች ጉዳት ለደረሰባው ወገኖች ድጋፍ በማድረግ እና ተፈናቃዮችን ወደ መጠለያ ጣብያዎች በማጓጓዝ በከፍተኛ ጫና ውስጥ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
ካሳለፍነው ሳምንት ሰኞ ጀምሮ በቀጠለው ጥቃት እስካሁን ወደ አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች ተፈናቅለዋል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ የግጭቱን መጠን ለመቀነስ ከአጋር አካላት ጋር በዲፕሎማሲያው መፍትሄዎች ዙርያ እየመከርን ነው ብለዋል፡፡
እንደ ሊባኖስ ጤና ሚንስትር መረጃ ከሆነ ሳምንት በተሻገረው ጥቃት ከ1300 በላይ ሰዎች ሲገደሉ ትላንት በቤሩት በተፈጸመ ጥቃት ብቻ 50 ሰዎች ሞተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሄዝቦላህ ወደ ሰሜናዊ እስራኤል የሚያስወነጭፋቸው ሮኬቶች መጠን እንዲጨምሩ አድርጓል፡፡
እስራኤል በበኩሏ በትላንትናው እለት በየመን የሀይል ማመንጫ ጣብያዎች ፣ በራስ ኢሳ እና ሁዳይዳ ወደቦች ላይ የአየር ጥቃት ሰንዝራለች፡፡
እነዚህ ስፍራዎች በቅርቡ ከየመን ወደ ቴልአቪቭ ሮኬት የተወነጨፈባቸው እንዲሁም ኢራን ለሁቲ ታጣቂዎች የጦር መሳርያ ድጋፍ የምታሸጋግርባቸው መሆናቸውን የእስራኤል መከላከያ ሀይል አስታውቋል፡፡
በበሌላ በኩል ኤቢሲ የተባለው የአሜሪካ መገናኛ ብዙሀን ከውስጥ ምንጭ አገኝሁት ባለው መረጃ ቴልአቪቭ በቅርቡ በደቡባዊ ሊባኖስ የምድር ላይ ጥቃት ልትፈጽም እንደምትችል ገልጿል፡፡
ይህ በእግረኛ ሀይል ይፈጸማል የተባለው ጥቃት ወደ ሊባኖስ ማዕከላዊ አካባቢዎች ዘልቆ የሚገባ ሳይሆን በድንበር አቅራቢያ የሄዝቦላህ መገኛ ናቸው በተባሉ ስፍራዎች ዘመቻዎችን የሚያከናውን ነው ተብሏል፡፡
የእስራኤል መከላከያ ጦር ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሌተናል ጄነራል ሄርዚ ሃሌቪ ባሳለፍነው ሳምንት በሰሜናዊ የእስራኤል ድንበር አቅራቢያ ለሚገኙ ወታደሮች ባደረጉት ንግግር፤ “የአየር ሀይሉ እየፈጸመ የሚገኝው ጥቃት ለእግረኛ ጦሩ መንገዶችን ለመጥረግ ነው፤ በቅርቡ ወደ ሊባኖስ ልንገባ እንችላለን” ማለታቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡