የሄዝቦላን መሪ ለመግደል ጥቅም ላይ ውሏል የተባለው "በንከር በስተር" ቦምብ ምን አይነት ነው?
በንከር በስተር ቦምብ 5000 ፖውንድ ክብደት አለው ተብሏል
"በንከር በስተር" ቦምቦች የበለጸጉት በአሜሪካ ሲሆን ከፍተኛ ምሽግን ወይም ከመሬት ስር የተደበቀ ነገርን ለማውደም ጥቅም ላይ ይውላል
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ እስራኤል የሄዝቦላውን መሪ በገደለችበት የአየር ጥቃት "በንከር በስተር" የተባለን አሜሪካ ሰራሽ ቦምብ ተጠቅማለች የሚል ክስ አቅርቧል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከቀናት በፊት በኒው ዮርክ በተካሄደው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እስራኤል 5000 ፖውንድ ክብደት ያላቸውን የአሜሪካ ቦምቦች ተጠቅማለች ብለዋል።
የእስራኤል ጦር የሄዝቦላን መሪ መግደሉን ያስታወቀው ባለፈው ቅዳሜ ነው። የጦሩ ቃል አቀባይ አቪቻይ አድሬ በቤሩት ከመኖሪያ ቤቶች ስር በሚገኘው የሄዝቦላ ማዕከላዊ ማዘዣ ጣቢያ ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት የቡድኑ መሪ ነስረላህ መገደሉን መግለጹ ይታወሳል።
ቲአርቲ የተባለው የቱርክ የቴሌቪዥን ጣቢያ የእስራኤሉን ቻናል 12 ጠቅሶ እንደዘገበው የእስራኤል አየር ኃይል እያንዳንዳቸው አንድ ቶን ክብደት ያለው ፈንጅ ያላቸውን 58 "በንከር በስተር" ቦምቦችን ጥሏል።
"በንከር በስተር" ቦምቦች የበለጸጉት በአሜሪካ ሲሆን ከፍተኛ ምሽግን ወይም ከመሬት ስር የተደበቀ ነገርን ለማውደም ጥቅም ላይ ይውላል።
ቦምቦቹ ከመሬት ውስጥ ያሉ ወታደራዊ ቦታዎችን፣ ማንኛውም የጦር መሳሪያ ሊያወድማቸው የማይችሉ ተቋማትን ኢላማ ለማድረግ ተብሎ ነው የተሰሩት።
በንከር በስተር ቦምቦች በዘመናዊ ጦርነት ውስጥ የጠላትን ይዞታዎች በማውደም ረገድ ጠቀሜታዎች እየጎላ መጥቷል። አለምአቀፍ ህግ እነዚህ ቦምቦች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ባይከለክልም፣ በመኖሪያ ቦታዎች መጠቀም ግን የጄኔቫ ኮንቬንሽንን ጨምሮ አለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ህግን የሚጥስ ነው።
ጋይድ ቦምብ ዩኒት 28 እና ዩኒት 37
ጋይድድ ቦምብ ዩኒት 28 የበለጸገው በ1991 በገልፍ ጦርነት ወቅት ሲሆን ጠንካራ የተባሉ የኢራቅን የመሬት ውስጥ ይዞታዎችን ለማፈራረስ ጥቅም ላይ ውሏል። ይህ ቦምብ 5000 ፖውንድ ገደማ ክብደት አለው። ቦምቡ በርካታ የውጭ ሽፋኖች ያሉት ሲሆን ከመፈንዳቱ በፊት ኮንክሪቶችን እና መሬትን ቀዶ እንዲያልፍ ያስችለዋል።
ጋይድድ ቦምብ ዩኒት 37 ከመሬት ስር ያሉ ወታደራዊ ይዞታዎችን ለመምታት የሚያስችል ነው። ከጋይድድ ቦምብ ዩኒት-37፣ ከጋይድድ ቦምብ ዩኒት 28 በተለየ መልኩ የአቅጣጫ መቆጣጠሪያ (ጂፒኤስ) የተገጠመለት እና በአስቸጋሪ የከባቢ አየር ሁኔታ ውስጥ ትክክለኛ ኢላማ መምታት የሚችል ነው።
ይህ ቦምብ እንደ ኢራን እና ሰሜን ኮሪያ ባሉ ከመሬት ስር ያሉ የኑክሌር ማበልጸጊያ ቦታዎችን ለመምታት የሚውሉ በአሜሪካ እጅ ያለ ወሳኝ መሳሪያ እንደሆነ ተገልጿል።
የበንከር ብምቦች ዋና ጥንካሬያቸው የመሬትን የላይኛው ክፍል ድርብርቦች(ሌየርስ)፣ ድንጋይ እና ኮንክሪት የመብሳት አቅሙ ነው። የቦምቦቹ መያዣዎች ከፍተኛ ጥንካሬ ካለው ቁሶች የተሰሩ ስለሆነ በጥልቀት ያለን ኢላማ እስከሚያገኙ ድረስ ጥሰው እንዲያልፉ ያስችላቸዋል።