በባንኮች የዶላር ምንዛሬ ዋጋ ከ24 ቀናት በፊት ከነበረበት በአማካይ የ47 ብር ጭማሪ አሳይቷል
ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ስርአት መከተል ከጀመረች 24 ቀናት ተቆጥረዋል።
ባንኮችም በማህራዊ ትስስር ገጻቸው የየእለቱን የውጭ ምንዛሬ ተመን ዝርዝር ይፋ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ነሃሴ 15 2016 የውጭ ሀገር ገንዘቦችን የሚገዛበትን እና የሚሸጥበትን ዋጋ ይፋ ሲያደርግ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ104.0834 ብር እየገዛ በ115.3244 ብር እየሸጠ መሆኑን አስታውቋል።
ባንኩ ባለፉት አራት ቀናት ያወጣው የውጭ ምንዛሬ ተመን ተመሳሳይ ነው።
ዳሸን ባንክም ትናንት ባወጣው የውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ ለውጥ ሳያደርግ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ104.2016 ብር እየተገዛ በ116.4798 ብር እየተሸጠ መሆኑን ባወጣው እለታዊ የምንዛሬ ተመን ይፋ አድርጓል።
ኦሮሚያ ባንክ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ104.7820 ብር እየተገዛ በ118.4037 ብር እየተሸጠ ይገኛል።
ንብ ባንክም የነሃሴ 14 2016ቱን የውጭ ምንዛሬ ተመን ያስቀጠለ ሲሆን አንድ የአሜሪካ ዶላር በ104.8562 ብር እየተገዛ በ117.4379 ብር እየተሸጠ ነው።