የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ስርአትን መሸከም የሚችልበት ሁኔታ ላይ አለመሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ገለጹ
ከትላንትናው እለት ጀምሮ ስራ ላይ የዋለው የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ፖሊሲ በገቢ ንግድ ላይ ከተመሰረተው ኢኮኖሚ ጋር እንደማይጣጣም ተነግሯል
ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ይፋ ማድረጓን ተከትሎ ከአይኤምኤፍ የ3.4 ቢሊዮን ዶላር ብደር አግታለች
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ ስርአት ከትናንት ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን በመወሰን ትልቅ የሚባል የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጥ አድርጓል።
ይህ ውሳኔ “ፊክስድ” በሚባለው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ብሄራዊ ባንኩ የውጭ ምንዛሬ ተመንን እየተመነ ገበያውን ለማረጋጋት የሚጥርበትን አካሄድ ሙሉ ለሙሉ የሚቀይር ነው፡፡
ከትላንት ሰኞ ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም ጀምሮ በመላው ሀገሪቱ ያሉ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ የሚሸጡትም ሆነ የሚገዙት ከደንበኞቻቸው ጋር በሚደረግ ድርድር እንዲሆን ተወስኗል፡፡
ገበያ መር ወይም “ፍሎቲንግ” በመባል የሚታወቀው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር በገበያው ውስጥ ባለው የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት እና አቅርቦት እንዲሁም ባንኮች እንዳላቸው የውጭ ምንዛሪ ክምችት የምንዛሪ ዋጋውን የሚተምኑበት አሰራር ነው፡፡
ጉዳዩ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያለ በርካታ ምርቶችን ከውጭ በማስገባት በገቢ ምርቶች ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ባላቸው ሀገራት ላይ አሉታዊ ጫና እንደሚኖረው የተለያዩ የምጣኔ ሀብት ምሁራን እና ተመራማሪዎች በመናገር ላይ ይገኛሉ፡፡
በገቢ እና በወጭ ንግድ መካከል ያለው የንግድ ሚዛን መዛባት ከፍተኛ በሆነበት በውጭ ምንዛሪ ላይ የሚተላለፍ እያንዳንዱ ውሳኔ በዋጋ ንረት እና በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ ቀላል እንዳልሆነ ይነገራል፡፡
በቅርቡ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ(ዶ/ር) የበጀት አመቱን አፈጻጸም በተመለከተ በምክር ቤት ተገኝተው ማብራርያ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት ፤ ሀገሪቱ ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸው ምርቶች የምታገኝው ገቢ 4 ቢሊየን ዶላር የማይሞላ ሲሆን በአንጻሩ በአመት ከ7 ቢሊየን ዶላር በላይ ለእዳ ክፍያ ፣ ለአፈር ማዳበርያ እና ለነዳጅ ወጪ ታደርጋለች፡፡
አል ዐይን አማረኛ መንግስት ተግባራዊ ያደረገው የገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ፖሊስ አስተዳደር ምን አንድምታ አለው ሲል ከምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
የፓን አፍሪካን ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ ኢንደስትሪ ዋና ዳይሬክተር እና የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ክቡር ገና “እኔ ስለዜናው ስሰማ ደንግጫለሁ፤ ምንም እንኳን መንግስት ከሚገኝበት የውጭ ምንዛሬ እጥረት አንጻር ውሳኔው ተጠባቂ ቢሆንም በዚህ ፍጥነት ተግባራዊ ይደረጋል ብየ አልጠበኩም። አሁን ባለው አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ዶላርን መልቀቅ ማለት ጥቂቶች እየተጠቀሙ ብዙሀኑ እንዲጎዳ መፍቀድ ነው” ይላሉ፡፡
ገበያ መር የውጭ ምንዛሪን ተግባራዊ ማድረግ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ችግር መፍትሄ አይደለም የሚሉት አቶ ክቡር መንግስት አሰራሩን ተግባራዊ ከማድረጉ በፊት መስራት የነበረበትን የቤት ስራዎች እና ቅድመ ዝግጅቶችን አሟልቷል ብየ አላምንም ብለዋል፡፡
እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች በቅድሚያ በመላ ሀገሪቱ ሰላምን ማረጋገጥ ፣ ቀጥሎም አምራች ዜጋን እና ሁኔታን መፍጠር ፣ ትናንሽ ንግዶች እና ትላልቅ ባለሀብቶች ያለባቸውን የብድር እና የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ምላሽ መስጠት ፣ በአቅርቦት እና በፍላጎት መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት እንኳን ባይቻል ለማቀራረብ ጥረት መደረግ ይኖርበት ነበር ነው የሚሉት፡፡
“በቀላሉ ለማስረዳት በ58 ብር አንድ ዶላር ገዝቶ ከውጭ ምርት የሚያስገባ ነጋዴ በ76 እና ከዛ በላይ በሆነ ምንዛሪ የሚገዛውን ምርት ሀገር ውስጥ አምጥቶ ሲሸጠው ገበያው ላይ የሚፈጠረውን ጫና አስበው”፡፡
የሀገሪቱ የንግድ ስርአት ቀናኢ አይደለም የሚሉት አቶ ክቡር ነጋዴው አይደለም ምንዛሬ ተለቆ በቂ ምርት ባለበትም ጊዜ 100 ፐርሰንት እና ከዛ በላይ የትርፍ ተመን አውጥቶ የሚሸጥ በመሆኑ የሸቀጦች ዋጋ ህዝቡ ካለው የመግዛት አቅም ጋር ሲወዳደር በብዙ እጥፍ እንዲጨምር የሚያደርግ ስለመሆኑ ነግረውናል፡፡
አክለውም “አብዘሀኛው የሀገሪቱ ዜጋ በቋሚ ገቢ የሚኖር ተቀጣሪ እና የቀረውም በአነስተኛ ንግዶች ላይ ተሰማርቶ በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደር ነው፤ ይህ በእንዲህ እንዳለ ገቢህ ሳይጨምር የገንዘብ የመግዛት አቅም ተዳክሞ በዛ ላይ ሸቀጦች ዋጋ ሲንር የገበያ መናጋትን ሊፈጥር እንደሚችል መገመት ቀላል ነው”፡፡
“በዶላር ምንዛሪ መጨመር ምክንያት የሚዘዋወረው ገንዘብ መጨመር በራሱ በገበያ ውስጥ ካለው የምርት እጥረት ጋር የማይጣጣም በመሆኑ ያልተገባ የዋጋ ንረት እና ከፍተኛ የምርት እጥረትን ሊያስከትል የሚችል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ገበያው የሚዘወረው በጥቂት አካላት ቁጥጥር ስር ከመሆኑ የተነሳ ሊመነጭም ይችላል”::
ሌላኛው የኢኮኖሚ ባለሙያ ዋሲሁን በላይ የምንዛሪ አስተዳደሩን ኢኮኖሚ ጠቀሜታው ታስቦ ብቻ የተደረገ ሳይሆን ከአበዳሪ አካላት መንግስት ከደረሰበት የበረታ ጫና ተነስቶ የወሰነው እንደሚሆን አምነት አላቸው፡፡
አያይዘውም ውሳኔው ከብድር ጫና እና ከመክፈል አቅም ጋር በተገናኝ በራሱ በመንግስት ላይ ከሚፈጥረው ጫና ጋር አስተሳስረው ያነሱታል፡፡
“መንግስት ከውጭ የተበደራቸውን እዳዎች ለመክፈል የውጭ ምንዛሪ ያስፈልገዋል። የተበደራቸው ብድሮች የቱንም ያህል ወለዳቸው ዝቅተኛ ቢሆን በሀገር ውስጥ ያለው የምንዛሪ ተመን በጨመረ ቁጥር አንድ ዶላር በ50ዎቹ ውስጥ እያለ የተበደረው ገንዘብ ወደ 70 እና ከዛ በላይ ሲጠጋ ዶላር ለመግዛት የሚወጣውን ብር ስለሚጨምረው የእዳው መጠን ከወለዱ ውጭ በእጥፍ እንዲያድግ ሊያደርግ ይችላል” ይላሉ፡፡
ይህን ለማስተካከል ወደ ብር ህትመት የሚገባ ከሆነ ደግሞ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ጫናን በህዝብ እና በመንግስት ላይ ሊያስከትል የሚችል ነው፡፡
አቶ ዋሲሁን መንግስት የውጭ ምንዛሬን በአንድ ጊዜ በገበያ እንዲወሰን ከመፍቀድ ይልቅ መጠኑ የታወቀ እና ለአመታት ቋሚ ሆኖ የሚዘልቅ የገንዘብ ማዳከመን ተግባራዊ ቢያደርግ ቢያንስ የገበያወን ሁኔታ ለመቆጣጠር እና ቀስ በቀስም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሪ የሚፈጥረውን ጫና ማቃለል እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
መንግስት አሰራሩ በግልጽ በኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረውን ጫና አምኗል የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው ይህን ተጽእኖ ለመቋቋም ደሞዝ ጭማሪ እና ድጎማን ተግባራዊ አደርጋለሁ ማለቱ ዘላቂ መፍትሄ እንደማይሆን ያነሳሉ፡፡
መንግስት ከ10 ቢሊየን ዶላር በላይ ከአለም ባንክ እና ከአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እንደሚያገኝ ሲያስታውቅ በገበያ ውስጥ የሚፈጠረውን ቀውስ ለማረጋጋት እንደሚያውለው ገልጿል፡፡
አቶ ዋሲሁን አክለውም “መንግስት እስከመቼ እየደጎመ ሊዘልቅ እንደሚችል አላውቅም መሰረታዊ የሆኑ የምርት እና የምርታማነት እንዲሁም የብድር ጥያቄ አቅርቦቶችን መፍታት እና ዜጎች ለኢኮኖሚው ጉልበት የሚሆኑበትን እድል ካልፈጠረ ባለህበት እርገጥ ነው የሚሆነው”፡፡
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ክቡር ገና ከዚህ ጋር በሚስማማው ሀሳባቸው ኢንቨስተሮች እና የግል ሴክተሩ በተለይ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መተካት ላይ እንዲሰማራ ከመንግስት ፕሮጀክቶች ላይ ተቀንሶም ቢሆን ገንዘብ ሊለቀቅለት ይገባል ይላሉ፡፡
ከዚህ ባለፈም የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለመሳብ ታሳቢ አድርጎ የተወሰነው ውሳኔ በዘላቂ ሰላም ካልታገዘ የትኛውም ባለሀብት ፋብሪካ አቁሞ ምርት ለማምረት አይፈቅድም ነው የሚሉት፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በገበያ የሚወሰን የውጭ ምንዛሪ አስተዳደርን ተግባራዊ ሲያደርግ፤ የውጭ ምንዛሬ በሚያስገኝ ስራ የተሰማሩ ሰዎችን መጥቀም፣ የውጭ ምንዛሬው በተገቢው መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ማድረግ፣ በሀገር ውስጥ የሚያመርቱ ኢንዱሰትሪዎች እንዲበረታቱ እና የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ ሀገር ውስጥ ኢንዲገቡ ማበረታታት እና ህጋዊ ያልሆኑ የውጭ ምንዛሬን ግብይትን ማስቀረት የማሻሻያው ዋና ዋና ጠሜታዎች ናቸው ብሏል፡፡
መንግስት ከአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ጋር ብድር ለማግኘት ረዘም ላለ ጊዜ ድርድር ሲያደርግ ቆይቷል።
አይኤምኤፍ ለኢትዮጵያ ብድር ለመስጠት፣ የኢትዮጵያ መንግሰት የፖሊሲ ማሻሻያ እንዲያደርግ ሲጠይቅ እንደነበር እና ከእነዚህ ውስጥ ዋነኛው በገበያ የሚወሰን የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል።
መንግስት ይህን የውጭ ምንዛሬ ስርአት ይፋ ባደረገበት በትናንትናው አይኤምኤፍ የ3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር ማድረጉን አስታውቋል።