የአለም ባንክ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የአፍሪካ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ያካተታቸው ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
የ20 የአፍሪካ ሀገራትን ዝርዝር ይፋ ያደረገው ባንኩ ኢትዮጵያን ከዝርዝሩ ውስጥ አካቷታል
ዝርዝሩ የዜጎች ገቢ መቀነስ እና ሀገራቱ ለመሰረት ልማት እንዲሁም ለአስፈላጊ ፕሮጄክቶች ያለባቸውን የገንዘብ እጥረት ከግምት ውስጥ አስገብቷል
የአለም ባንክ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የአፍሪካ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ያካተታቸው ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
የአለም ባንክ በ2024 ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የአፍሪካ ሀገራትን ዝርዝር አውጥቷል፡፡
አለም አቀፍ ተጽእኖ ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ፣ የኑሮ ውድነት ፣ ሙስና እና ግጭት ሀገራት መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው ሀገራት ደረጃ ውስጥ ለመካተት የሚያደርጉትን ግስጋሴ እንደጎተተው ባንኩ አስታውቋል፡፡
ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት ለትምህርት ፣ ለጤና ፣ ለመሰረት ለማት እና ለሌሎች መንግስታዊ ወጪዎች ያለባቸው የገንዘብ እጥረት በአመቱ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ከዚህ ባለፈም የዜጎች የኑሮ ደረጃ ዝቅተኛነት ለመኖር መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት የሚያደርጉት ጥረት ፈታኝ ስለማድረጉ ነው ባንኩ ባወጣው ሪፖርት ይፋ ያደረገው፡፡
ዜጎች ገቢያቸው ባልጨመረበት ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ እያሻቀበ የሚገኝው የዋጋ ንረት የሰዎች ኑሮ እንዳይሻሻል ምክንያት ሆኗል፡፡
በሀገራቱ የሚገኝው የድህነት ደረጃ ፣ የገቢ አለመመጣጠን ፣ በሀምታም እና ድሆች መካከል የሚገኝው የኑሮ ልዩነት እና የሸቀጦች ዋጋ መኖር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች እንዲበረክቱ አድርጓል፡፡
የምግብ ሸቀጦችን ጨምሮ በርከት የሚሉ ግብአቶችን ከውጭ ሀገራት የሚያስገቡት እነዚህ ሀገራት በአለም አቀፍ ደረጃ ያለው የገበያ አለመረጋጋት የሚደርስባቸው ተጽዕኖ በዜጎቻቸው እና በምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጫናን እያሳደረ ይገኛል፡፡
የውጭ እዳ ጫና እንዲሁም በሀገራቱ የሚገኙ የሰላም መደፍረሶች እና ግጭቶች በዝቅተኛ ገቢ ውስጥ እንዲዘልቁ ካስገደዱ ተጨማሪ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
የአለም ባንክ በዚህ ጫና ውስጥ እያለፉ ይገኛሉ በሚል ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን 20 የአፍሪካ ሀገራት ዝርዝር አውጥቷል፡፡
ኢትዮጵያ ፣ ኤርትራ ፣ ቡርኪና ፋሶ ፣ ሱዳን ፣ ሶማሊያ ፣ ብሩንዲ ፣ ቻድ ፣ ኡጋንዳ ፣ ዲአር ኮንጎ ፣ ጋምቢያ ፣ ላይቤሪያ ፣ ጊኒ ቢሳው ፣ ማዳጋስካር ፣ ማላዊ ፣ ማሊ ፣ ሞዛምቢክ ፣ ኒጄር ፣ ሩዋንዳ ፣ ደቡብ ሱዳን እና ቶጎ ይገኙበታል፡፡
ምንም እንኳን ሀገራቱ በዝቅተኛ ገቢ ውስጥ የሚገኙ ቢሆንም ፖለቲካዊ መረጋጋትን አስፍነው ምርታማነት ላይ የሚሰሩ ከሆነ የበርካታ ወጣቶች እና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤቶች በመሆናቸው ሁኔታዎችን በቅርብ ጊዜ የመቀየር አቅም እንዳላቸው ባንኩ በሪፖርቱ አካቷል፡፡