የግል ንግድ ባንኮች የ1 ዶላርን እስከ 104 ብር እየገዙ እስከ 117 ብር እየሸጡ ነው
ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኗን ተከትሎ ባንኮች አዲሱን የምንዛሬ ተመን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ባንኮች በማህራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት የነሃሴ 14 2016 የውጭ ምንዛሬ ተመን ዝርዝር ላይ ከሳንቲሞች እስከ 7 ብር የሚደርስ የዋጋ ልዩነት ታይቶባቸዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ነሃሴ 14 2016 የውጭ ሀገር ገንዘቦችን የሚገዛበትን እና የሚሸጥበትን ዋጋ ይፋ ሲያደርግ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋን ትናንት ሲገዛበት ከነበረው ጋር ተመሳሳይ በሆነ ዋጋ በ104.0834 ብር እየገዛ ይገኛል። መሸጫው ላይም በተመሳሳይ ጭማሪ ሳያደርግ 115.3244 ብር እየሸጠ ይገኛል።
የእንግሊዝ ፓውንድ በ128.1856 ብር እየገዛ በ142.6853 ብር እንደሚሸጥም አስታውቋል።
ዳሸን ባንክ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ104.2016 ብር እየተገዛ በ116.4798 ብር እየተሸጠ መሆኑን ባወጣው እለታዊ የምንዛሬ ተመን ይፋ አስታውቋል።
በፀሃይ ባንክ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ104.3124 ብር እየተገዛ በ116.8299 ብር እየተሸጠ መሆኑን ባወጣው እለታዊ የምንዛሬ ተመን ይፋ አድርጓል።
ንብ ባንክ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ104.8562 ብር እየተገዛ በ117.4379 ብር እየተሸጠ መሆኑን ባወጣው እለታዊ የምንዛሬ ተመን ይፋ አድርጓል።