የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመደበኛ የምንዛሬ ተመን 1 ዶላር በ108 ብር ገዝቶ በ119 ብር እየሸጠ ነው
ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኗን ተከትሎ ባንኮች አዲሱን የምንዛሬ ተመን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
የ2017 አዲስ ዓመት አስመልክቶም ባንኮች በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያውን በባንኮች አማካኝነት ገንዘብ እንዲልኩ የሚያበረርታታ ተመን እያወጡ ነው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች በኩል የሚላክን ገንዘብ ከባንኩ ለሚቀበሉ ደንበኞቹ ተጨማሪ የ6.82 በመቶ የበዓል ስጦታ እንደሚሰጥ አስታውቋል።
ባንኩ ዛሬ መስከረም 6 2017 ዓ.ም መደበኛ የውጭ ሀገር ገንዘቦችን የሚገዛበትን እና የሚሸጥበትን ዋጋ ይፋ ሲያደርግ ባለፉት ቀናት ያወጣውን ተመን አስቀጥሏል፤ 1 ዶላርን በ108.0728 ብር እየገዛ በ119.9068 ብር እየሸጠ ይገኛል።
እስከ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ የሚላክን አንድ የአሜሪካ ዶላር በ125 ብር እንደሚመነዝር ያስታወቀው ንብ ባንክም መደበኛውን (እለታዊ የምንዛሬ ተመን) ይፋ አድርጓል።
በዚህም ባንኩ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ107.8729 ብር እየገዛ በ120.8176 ብር እየተሸጠ መሆኑን ገልጿል።
ዳሸን ባንክ በዓልን ምክንያት በማድረግ ልዩ የምንዛሬ ዋጋ ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ በዚህም በሃዋላ የሚላክ 1 ዶላርን ከመደበኛው የምንዛሬ ዋጋ ላይ እስከ 16 በመቶ ጉርሻ እንደሚሰጥ ማሳወቁ ይታወቃል።
ባንኩ በመደበኛ የምንዛሬ ዋጋው ደግሞ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ108.0703 ብር እየገዛ በ121.5791 ብር እየሸጠ መሆኑን ነው ባወጣው እለታዊ የምንዛሬ ተመን ይፋ ያደረገው።
ኦሮሚያ ባንክም በዓልን ምክንያት በማድረግ ከውጪ በሃዋላ የተላከ አንድ የአሜሪካ ዶላርን ከእለታዊ ተመን በተጨማሪ 17 በመቶ ጉርሻ እንደሚሰጥ እና በዚህም 1 ዶላርን በ126+ ብር እንደሚመነዝር ማስታወቁ ይታወሳል።
ባንኩ የዛሬ የመስከረም 6 2017 መደበኛ የምንዛሬ ተመኑን ይፋ ሲያደርግ 1 የአሜሪካ ዶላር በ108.0920 ብር እየገዛ በ122.1440 ብር እየሸጠ መሆኑን ነው የጠቆመው።