የሪፐብሊካን እጪ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግድያ ሙከራ ሲደረግባቸው በ2 ወራት ውስጥ ለሁለኛ ጊዜ ነው
የአሜሪካ ቀድሞ ፕሬዝዳንት እና የሪፐብሊካን እጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ የግድያ ሙከራ ተደረገባቸው።
ዶናልድ ትራምፕ የግድያ ሙከራው የተደረገባቸው በፍሎሪዳ በሚገኘው የጎልፍ መጫወቻ ሜዳቸው ላይ መሆኑን ኤፍ.ቢ.አይ አስታውቋል።
የግድያ ሙከራው በተፈጸመበት ወቅትም ዶናልድ ትራምፕ በፓልም ባህር ዳርቻ ላይ ጎልፍ እየተጫወቱ ነበር ተብሏል።
ዶናልድ ትራምፕ ላይ ያነጣጠረ ነበር የተባለው የግድያ ሙከራው በሚስጥራዊ ደህንነት አባላት መክሸፉን ነው ኤፍ.ቢ.አይ ያስታወቀው።
በርካታ የአሜሪካ የሚስጥራዊ ደህንነት አባላት ከጎልፍ መጫወቻው አጠገብ ባለው ጫካ ውስጥ በነበረ እና መሳሪያ የታጠቀ ሰው ላይ ሲተኩሱ መታየታቸውም ተነግሯል።
ግድያው ሊፈጽም ነበር በሚል የተጠረጠረው ግለሰብ ትራምፕ ጎልፍ ከሚጫወቱበት መቶ ሜትሮች ርቀት ላይ እንደነበረም ነው የተገለጸው።
ተጠርጣሪው ኤኬ-47 ዓይነት ጠብመንጃ እና ሌሎች ቁሳቁሶችን በቦታው በመተው በተሽከርካሪ የሸሸ ቢሆንም፤ በኋላ ላይ በተደረገ ክትትል በቁጥጥር ስር ውሏል።
በርካታ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን በግድያ ሙከራው የተጠረጠረው ግለሰብነዋሪነቱ በሃዋይ የሆነ የ58 ዓመቱ ራያን ዋስሌይ ሩት እንደሆነ ማረጋገጣቸውን ዘግበዋል።
የቀድሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከተደረገባቸው የግድያ ሙከራ ተርፈው “ደህንነቱ የተጠበቀ” ቦታ እንደሚገኙ የአሜሪካ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
“ለተጨነቃችሁልኝ እና መልካም ምኞታችሁን የገለጻችሁልኝን በሙሉ አመሰግናለሁ” ያሉት ትራምፕ፤ ለደጋፊዎቻቸው በላኩት የኢሜይል መልዕክት “ደህና ነኝ” ብለዋል።
ትራምፕ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይም “ምንም ነገር ቢመጣ ወደኋላ አይመልሰኝም፤ በፍፁም እጄን አልሰጥም” ሲሉ ፅፈዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን “ዶናልድ ትራምፕ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው በመትረፋቸው እፎይታ እንደተሰማቸው” ገልጸዋል።
የሪፐብሊካን እጩ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግድያ ሙከራ ሲደረግባቸው በ2 ወራት ውስጥ ለሁለኛ ጊዜ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም በፔንሲልቫኒያ የምርጫ ቅስቀሳ ላይ እያሉ በተተኮሰባቸው ጥይት ጆሮዋቸው ላይ መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸው ነበር።
ሁለቱም የግድያ ሙከራዎች ህዳር 5 ለሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የእጩዎችን ደህንነት መጠበቅ ፈታኝ ደረጃ ላይ መድረሱን ያመለክታል።