በየቀኑ ሚሳኤል በሚተኮስባት ዩክሬን ኢትዮጵያዊያን እንዴት እየኖሩ ነው?
ኢትዮያውያኑ “ስጋት በሁሉም ስፋራ አለ፤ ጦርነቱ ሩቅም ሆነ ቅርብ የመመታት እድል አለ” ይላሉ
የሩሲያ ጥቃት ማስጠንቀቂያ መልክት ሲደርስ ኢትዮጵያዊያኑን ጨምሮ ሁሉም ዜጋ መደበቂያ ፍለጋ እንደሚሮጡ ሰምተናል
በየቀኑ ሚሳኤል በሚተኮስባት ዩክሬን ኢትዮጵያዊያን እንዴት እየኖሩ ነው?
ወልጫፎ ነጋሽ ይባላል፡፡ አዲስ አበባ፣ ቡታጅራ እና ዳለቻ ከተሞች ደግሞ የልጅነት ህይወቱን ያሳለፈባቸው ናቸው፡፡ ወደ ዩክሬን ሪፐብሊክ የስኮላርሽፕ እድል እንዲያገኝ መሰረት የሆነውን ትምህርት የተማረው ደግሞ ኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት ነው፡፡
በቀድሞ የሶቪየት ህብረት ጊዜ ማለትም ከ38 ዓመት በፊት ወደ ዩክሬን እንደተጓዘ የሚናገረው ወልጫፎ በሚቲዮሮሎጂ ሁለተኛ ድግሪውን ከሰራ በኋላ በዚያው ዩክሬን እየኖረ ይገኛል፡፡
ትምህርቱን በኦዴሳ ከተማረ በኋላ ወደ ሀገሪቱ መዲና ኪቭ በመምጣት እየኖረ መሆኑን የሚናገረው ወልጫፎ ባለትዳር እና የአንድ ሴት ልጅ አባትም ነው፡፡
ህይወት በዩክሬን እንዴት ነው? ብለን ላነሳንለት ጥያቄ ዩክሬናዊያን ደግ ህዝቦች ናቸው ለ38 ዓመታት ስኖር አንድም ቀን መጥፎ ነገር አጋጥሞኝ አያውቅም ነበር ብሏል፡፡
ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ህይወትን እንዴት እየቀጠላችሁ ነው?
“ጦርነቱ በዚህ ሀገር አቆጣጠር የካቲት 20 ቀን 2022 ዓ.ም ላይ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ነበር የተቀሰቀሰው፡፡ በወቅቱ ከባድ የሆነ እና የመብረቅ አደጋ የመሰለ ድምጽ ከእንቅልፋችን ቀሰቀሰን፡፡
ወዲያው ሁላችንም በመስኮት ስንመለከት እኔ ከምኖርበት 500 ሜትር ርቀት ላይ ባለ አንድ የመኖሪያ ቤት ህንጻ ላይ የሮኬት ጥቃት መሰንዘሩን እና ለሶስት ቀናት የሚቆይ ልዩ ዘመቻ በሚል የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት መቀስቀሱን ሰማን” ሲል የመጀመሪያውን ክስተት ነግሮናል፡፡
ከፈረንጆቹ 2014 ጀምሮ በሁለቱ ሀገራት አዋሳኝ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ግጭቶች ቢኖሩም እንዲህ ግን ወደ ይፋዊ ጦርነት ያመራሉ ብለን አልጠበቅንም ነበር የሚለው ወልጫፎ ይህ ጦርነት የዩክሬናዊንን ኢኮኖሚ አድቅቋል ብሏል፡፡
“ስጋት በሁሉም ዩክሬን ስፍራ አለ፡፡ አራት ሚሊዮን ነዋሪ ያለባት እና እኔ የምኖርባት ኪቭ ከተማ ከጦር ግንባሮች ሩቅ ብትሆንም ሚሳኤሎች እና ሮኬቶች ግን ወደ ከተማዋ ይተኮሳሉ፡፡ ያለነው ከጦር ግንባር ሩቅ ቢሆንም የመመታት እድል አለ፡፡ የዩክሬን መንግስት የሩሲያ ሚሳኤል እና ድሮን ወደ ዩክሬን የአየር ክልል ሲገባ በሞባይል ስልክ እና የማስጠንቀቂያ ደወሎች እና በሌሎች የብዙሃን መገናኛዎች መልዕክት ይመጣል፡፡ ያኔ በፍጥነት ራሳችን ከጥቃት ለመጠበቅ ወደ ምድር ቤት እና ሌሎች ስፍራዎች እንደበቃለን፡፡ ይህ የእለት ተዕለት ስራችን ሆኗል፡፡ አሁን አሁን ሰዎች እየተላመዱት መጡና ዝም እሚሉ አሉ ያኔ ንጹሃን እየሞቱ ነው” ብሏል፡፡
ወልጫፎ አክሎም የአየር ጥቃት ማክሸፊያ ቢኖሩም ሁሉንም መትቶ መጣል ባለመቻሉ መሰረተ ልማቶች በመውደማቸው ኪቭ ከተማ መብራት በፈረቃ ነው እየተጠቀምን ያለነው፡፡ ምዕራባዊን በሚሰጧቸው የጀነሬተሮች ድጋፍ ምክንያት እጥረቱን ለመፍታት እየተሞከረ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ለኢትዮጵያን አስቸጋሪው ነገር በጦርነቱ ምክንያት የምርት እጥረት በማጋጠሙ የኑሮ ውድነት አለ እንዲሁም ጦርነቱ መቼ እንደሚቆም አናውቅም ይህ ያሳስበናል ብሏል ወልጫፎ፡፡
ስለ ኢትዮጵያ ምን ታስባለህ? ያልነው ወልጫፎ “ስለ ኢትዮጵያ ሳስብ አዝናለሁ፣ ሁሉንም ነገር በንቃት እከታተላለሁ፡፡ የትግራይ ጦርነት ነበር፡፡ አሁን ደግሞ መንግስት ከፋኖ እና ሸኔ ታጣቂዎች ጋር እየተዋጋ ነው፡፡ ይህ ጦርነት ህዝብን እየጎዳ ነው፡፡ ጦርነት አውዳሚ ነው ማንንም አይጠቅምም ነገሩ በድርድር እንዲፈታ ምኞቴ ነው፡፡ በዘር ፖለቲካ አላምንም፣ ማንም ሰው በፈለገው ቦታ ተዘዋውሮ እንዲሰራ እና ሀብት እንዲያፈራ እፈልጋለሁ፡፡ በአዲሱ የ2017 ዓመት ይህ ለኢትዮጵያዊያን እንዲሳካ እመኛለሁ” ብሏል፡፡
ሌላኛው በዩክሬን የሚኖረው ኢትዮጵያዊው አስተያየት ሰጪ ኢምቦሪ መሀመድ ይባላል፡፡ በምስራቅ ካርኪቭ በምትገኘው ካርኪቭ መኖር ከጀመረ ሁለት ዓመት እንደሆነው ተናግሯል፡፡
“እኔ ከባድ ጦርነት ከሚደረግባቸው ቦታዎች መካከል በአንዱ ነው የምኖረው፡፡ ይህን ቃለ መጠይቅ ከጨረስን በኋላ ብዙ ነገሮች ሊቀያየሩ ይችላሉ፣ የድሮን እና ሌሎች ጥቃቶች አረፍት የላቸውም የደህንነት ማስጠንቀቂያዎች በዝተው ስልችት ብሎን ተስፋ ቆርጠናል” ብሏል፡፡
ለምን የተሻለ ደህንነት ወዳለበት ስፍራ አትጓዝም? በሚል ላቀረብንለት ጥያቄ “የጦር ግምባሩ በመብዛቱ ምክንያት ወደ የትኛውም አካባቢ መንቀሳቀስ የበለጠ ለጥቃት ያጋልጣል፣ ከሁለት ዓመት በፊትም ኢትዮጵያ ነበርኩ፡፡ ከባድ ጦርነት በነበረበት አካባቢ ነበር ስኖር የነበረው፣ ከጦርነት ወደ ጦርነት ሆኗል ህይወቴ፡፡ ከኢትዮጵያ ይልቅ ዩክሬን የተሻለ ደህነነት ይሰማኛል“ ሲልም ተናግሯል፡፡
“ዩክሬን ከኢትዮጵያ የተሻለ ነገር አድርጋልኛለች፣ ለቅቄ መሄድ የማልፈልገውም ለዚህ ነው፤ ከባዱ ነገር ቀዝቃዛ ወራቶች እየመጡ መብራት ባለመኖሩ ያኔ ነው ምን እንደምንሆን አላውቅም” ሲልም አክሏም ኢምቦሪ፡፡
ለጥቂት ቀናት በሚል የተጀመረው የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት ሶስተኛ ዓመቱ ላይ የሚገኝ ሲሆን በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ እዚህ ደርሷል፡፡
ዩክሬን ከሩሲያ የሚደርስባትን የአየር ላይ ጥቃቶች ለማክሸፍ በሚል ከምዕራባዊን ሀገራት ኤፍ-16 የተሰኘው የውጊያ አውሮፕላን እንዲሰጣት ከጠየቀች በኋላ ሀገራት ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
አሁን ደግሞ ዩክሬን የረጅም ርቀት ሚሳኤል ድጋፍ እንዲደረግላት እና በሩሲያ ምድር ጥቃት ማድረስ እንድትችል ሀገራት ይሁንታ እንዲሰጧት እየጠየቀች ሲሆን የተወሰኑ ሀገራት ሲፈቅዱ የተወሰኑት ደግሞ በመቃወም ላይ ናቸው፡፡
ፕሬዝዳንት ፑቲን በበኩላቸው የኔቶ ሀገራት ዩክሬን በረጅም ሚሳኤሎች ሩሲያን እንድታጠቃ ከፈቀዱ የቀጥታ ጦርነት ከኔቶ ጋር ሊጀመር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡