ዛሬ መስከረም 16 ባንኮች 1 ዶላርን በስንት ብር እየመነዘሩ ነው?
የግል ንግድ ባንኮች 1 ዶላርን እስከ 112 ብር እየገዙ፤ እስከ 126 ብር እየሸጡ ይገኛሉ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሐዋላ የተላከ ገንዘብ ላይ በእያንዳንዱ ዶላር በእለቱ ምንዛሬ ላይ ተጨማሪ 8 ብር ስጦታ እሰጣለሁ ብሏል
ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኗን ተከትሎ ባንኮች አዲሱን የምንዛሬ ተመን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
የ2017 አዲስ ዓመት አስመልክቶም ባንኮች በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያውን በባንኮች አማካኝነት ገንዘብ እንዲልኩ የሚያበረርታታ ተመን እያወጡ ነው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች በኩል የሚላክን ገንዘብ ከባንኩ ለሚቀበሉ ደንበኞቹ ከዕለቱ የውጭ ምንዛሬ ተመን በተጨማሪ በእያንዳንዱ የአሜሪካ ዶላር ላይ ተጨማሪ 8 ብር ስጦታ እሰጣለሁ ብሏል።
ባንኩ ዛሬ መስከረም 16 2017 ዓ.ም መደበኛ የውጭ ሀገር ገንዘቦችን የሚገዛበትን እና የሚሸጥበትን ዋጋ ይፋ ሲያደርግ የመግዣ ዋጋውን የትናንቱን አስቀጥሏል። በዚህም አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ112.3957 ብር እየገዛ በ123.6353 ብር እየሸጠ ይገኛል።
ዳሽን ባንክ በዓልን ምክንያት በማድረግ ልዩ የምንዛሬ ዋጋ ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ በዚህም በሃዋላ የሚላክ 1 ዶላርን ከመደበኛው የምንዛሬ ዋጋ ላይ እስከ 16 በመቶ ጉርሻ እንደሚሰጥ ማሳወቁ ይታወቃል።
ባንኩ በመደበኛ የምንዛሬ ዋጋው ደግሞ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ112.3989 ብር እየገዛ በ126.4488 ብር እየሸጠ መሆኑን ነው ባወጣው እለታዊ የምንዛሬ ተመን ይፋ ያደረገው።
ኦሮሚያ ባንክም በዓልን ምክንያት በማድረግ ከውጪ በሃዋላ የተላከ አንድ የአሜሪካ ዶላርን ከእለታዊ ተመን በተጨማሪ 17 በመቶ ጉርሻ እንደሚሰጥ እና በዚህም 1 ዶላርን በ126+ ብር እንደሚመነዝር ማስታወቁ ይታወሳል።
ባንኩ የዛሬ የመስከረም 16 2017 መደበኛ የምንዛሬ ተመኑን ይፋ ሲያደርግ 1 የአሜሪካ ዶላር በ112.3988 ብር እየገዛ በ127.0106 ብር እየሸጠ መሆኑን ነው የጠቆመው።
እስከ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ የሚላክን አንድ የአሜሪካ ዶላር በ125 ብር እንደሚመነዝር ያስታወቀው ንብ ባንክም መደበኛውን (እለታዊ የምንዛሬ ተመን) ይፋ አድርጓል።
በዚህም ባንኩ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ110.8181 ብር እየገዛ በ124.1163 ብር እየተሸጠ መሆኑን ገልጿል።