የእስራኤል እና የሊባኖስ ወታደራዊ አቅም በንጽጽር ምን ይመስላል?
ከጋዛው ጦርነት በኋላ በሄዝቦላህ እና እስራኤል መካከል ያለው ጦርነት ከሰሞኑ ከፍ ብሎ ታይቷል
የእስራኤል ወታደራዊ አቅም ከሊባኖስ አንጻር በበዙ እጥፍ ብልጫ ያለው ነው
የእስራኤል እና የሊባኖስ ወታደራዊ አቅም በንጽጽር ምን ይመስላል?
የጋዛውን ጦርነት ተከትሎ የመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ወደ ሁሉን አቀፍ አካባቢያው ግጭት የማምራት ስጋት ከቀን ወደ ቀን እያየለ ይገኛል፡፡
በሊባኖስ የሚንቀሳቀሰው በምዕራባውያን በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሄዝቦላህ ከእስራኤል ጋር የገባበት ውጥረት እያደገ መጥቶ ሁለቱ ወገኖች በሚሳይል እና በአየር በከፍተኛ ደረጃ ተኩስ እየተለዋወጡ ነው፡፡
እስካሁን ባለው ሁኔታ የሊባኖስ ብሔራዊ መከላከያ ጦር በሄዝቦላህ እና በእስራኤል ግጭት ውስጥ አለተሳተፈም፡፡
የሀገራት ወታደራዊ አቅም ላይ መረጃ እና ትንተና የሚያወጣው ግሎባል ፋየር ፓዎር የሊባኖስን እና የእስራኤል ወታደራዊ አቅምን በተመለከተ ባወጣው መረጃ የሰው ሀይል ቁጥር ፣ ወታደራዊ ተሸከርካሪዎች ፣ ታንክ እና ሌሎችንም የጦር መሳርያዎች በንጽጽር ውስጥ አካቷል፡፡
ወታደራዊ ቁጥርን በተመለከተ እስራኤል 170 ሺህ ወታዶሮች ሲኖሯት ሊባኖስ በበኩሏ 60 ሺህ የጦር አባላትን ይዛለች፡፡
በተጠባባቂ ወታደር ቁጥር ደረጃም ቢሆን 456 ሺህ ተጠባባቂ ጦር ያላት ቴልአቪቭ 35 ሺህ ተጠባባቂ ጦር ካላት ሊባኖስ በብዙ እጥፍ ትበልጣለች፡፡
ፓራሚሊታሪ ወይም ፈጥኖ ደራሽ በሚበለው ሀይል ቁጥር ሊባኖስ 60 ሺህ እስራኤል ደግሞ 35ሺህ አባላቶች አሏቸው፡፡
ወታደራዊ በጀትን በተመለከተ በቀጠናው ከፍተኛ ገንዘብን ለመከላከያ ከሚያፈሱ ሀገራት መካከል የምትመደበው ቴልአቪቭ አመታዊ ወታደራዊ በጀቷ 24.4 ቢሊየን ይጠጋል፤ በአንጻሩ ቤሩት 995 ሚሊየን ዶላር ነው መከላከያዋ ላይ ፈሰስ የምታደርገው፡፡
641 አውሮፕላኖችን የታጠቀው የእስራኤል አየር ሀይል ከእነዚህ ውስጥ 241 የሚሆኑት የውግያ አውሮፕላኖች እንዳሉት መረጃው ያመላክታል፡፡
81 አውሮፕላኖች 8 የአየር ማረፍያዎች ያሏት ሊባኖስ በበኩሏ ምንም የውግያ ጄት የላትም፡፡
በወታደራዊ ተሸከርካሪዎች ፈርጣማ አቅም ያላት እስራኤል በጋዛው ጦርነት በምድር ላይ ባደረገቻቸው ውግያዎች በስፋት ታንኮችን ጥቅም ላይ ስታውል ተስተውላለች፡፡
በዚህም ሀገሪቱ 1370 ታንክ እና 43 ሺህ 407 የታጠቁ ተሸከርካሪዎች ባለቤት ነች፡፡ ቤሩት ደግሞ 204 ታንኮች እና 4522 የታጠቁ ተሸከርካሪዎችን ይዛለች፡፡
በአንጻሩ በባህር ሀይል 69 የውግያ መርከቦችን የታጠቀችው ሊባኖስ 67 መርከቦች ካሏት እስራኤል ትበልጣለች፡፡