በአዲሱ ዓመት መስከረም 2 2017 የባንኮች የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ምን ይመስላል?
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1 ዶላር በ108 ብር እየገዛ፤ በ119 እየሸጠ ይገኛል
ባንኮች አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በሃዋላ የሚላክ 1 ዶላርን እስከ 125 ብር እየመነዘሩ ነው
ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኗን ተከትሎ ባንኮች አዲሱን የምንዛሬ ተመን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
የ2017 አዲስ ዓመት አስመልክቶም ባንኮች በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያውን በባንኮች አማካኝነት ገንዘብ እንዲልኩ እየጠየቁ ነው።
ዲያስፖራው በህገወጡ (ጥቁር ገበያ) ከመላክ ይልቅ ህጋዊውን መንገድ እንዲመርጥ የሚያበረታታ ተመንም እያወጡ ሲሆን፤ ባንኮች በማህራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት የመስከረም 2 2017 የውጭ ምንዛሬ ተመን ዝርዝር ላይ የዋጋ ልዩነት ታይቶባቸዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ ዓመትን ምክንያ በማድረግ በዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች በኩል የሚላክን ገንዘብ ከባንኩ ለሚቀበሉ ደንበኞቹ ተጨማሪ የ6.82 በመቶ የበዓል ስጦታ እንደሚሰጥ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ መስከረም 2 2017 ዓ.ም መደበኛ የውጭ ሀገር ገንዘቦችን የሚገዛበትን እና የሚሸጥበትን ዋጋ ይፋ ሲያደርግ ዶላር መግዣ ዋጋን ከሰሞኑ ሲገዛበት በነበረበት ዋጋ ማለትም 1 ዶላርን በ108.0728 ብር እየገዛ ይገኛል። መሸጫው ላይም ጭማሪ ሳያደርግ 119.9068 ብር እየገዛ ይገኛል።
የእንግሊዝ ፓውንድ በ135.5141 ብር እየገዛ በ151.1231 ብር እንደሚሸጥም አስታውቋል።
ንብ ባንክ እስከ መስከረም 30 2017 የሚቆይ ልዩ የውጭ ምንዛሬ ተመን ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፥ በዚህም እስከ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ የሚላከውን የውጭ ሀገር ገንዘብ አንዱን የአሜሪካ ዶላር በብር 125 ምንዛሪ እንደሚያስረክብ አስታውቋል።
ንብ ባንክ ዛሬ ይፋ ባደረገው መደበኛው የውጭ ምንዛሬ ተመኑ ደግሞ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ107.8729 ብር እየገዛ በ120.8176 ብር እየተሸጠ መሆኑን ገልጿል።
ዳሸን ባንክም በዓልን ምክንያት በማድረግ ልዩ የምንዛሬ ዋጋ ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ በዚህም በሃዋላ የሚላክ 1 ዶላርን ከመደበኛው የምንዛሬ ዋጋ ላይ እስከ 16 በመቶ ጉርሻ እንደሚሰጥ አስታውቋል።
ዳሸን ባንክ በመደበኛ የምንዛሬ ዋጋው ደግሞ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ108.0703 ብር እየገዛ በ121.05791ብር እየሸጠ መሆኑን ባወጣው እለታዊ የምንዛሬ ተመን አስታውቋል።