የጳጉሜ 1የባንኮች የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ምን ይመስላል?
የግል ባንኮች አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በሃዋላ የሚላክ 1 ዶላርን ከ115 እስከ 125 ብር እየመነዘሩ ነው
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መጠነኛ ጭማሪ በማደረግ 1 ዶላር በ107 ብር እየገዛ፤ በ119 እየሸጠ ይገኛል
ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኗን ተከትሎ ባንኮች አዲሱን የምንዛሬ ተመን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
አዲስ አመት መቃረቡን ተከትሎ ባንኮች በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያውን በባንኮች አማካኝነት ገንዘብ እንዲልኩ እየጠየቁ ነው።
ዲያስፖራው በህገወጡ (ጥቁር ገበያ) ከመላክ ይልቅ ህጋዊውን መንገድ እንዲመርጥ የሚያበረታታ ተመንም እያወጡ ሲሆን፤ ባንኮች በማህራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት የጳጉሜ 1 2016 የውጭ ምንዛሬ ተመን ዝርዝር ላይ የዋጋ ልዩነት ታይቶባቸዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ጳጉሜ 1 2016 የውጭ ሀገር ገንዘቦችን የሚገዛበትን እና የሚሸጥበትን ዋጋ ይፋ ሲያደርግ ዶላር መግዣ ዋጋን ትናት ሲገዛበት ከነበረበት ላይ ከ1 ብር በላይ ጭማሪ በማድረግ 1 ዶላርን በ107.7565 4 ብር እየገዛ ይገኛል። መሸጫው ላይም ጭማሪ በማድረግ 119.6097 ብር እየገዛ ይገኛል።
የእንግሊዝ ፓውንድ በ135.6525 ብር እየገዛ በ151.2714 ብር እንደሚሸጥም አስታውቋል።
ንብ ባንክ በትናንትናው እለት እስከ መስከረም 30 2017 የሚቆይ ልዩ የውጭ ምንዛሬ ተመን ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፥ በዚህም እስከ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ የሚላከውን የውጭ ሀገር ገንዘብ አንዱን የአሜሪካ ዶላር በብር 125+ ምንዛሪ እንደሚያስረክብ አስታውቋል።
ንብ ባንክ ዛሬ ይፋ ባደረገው መደበኛው የውጭ ምንዛሬ ተመኑ ደግሞ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ106.5938 ብር እየተገዛ በ119.3850 ብር እየተሸጠ መሆኑን ገልጿል።
ወጋገን ባንክ እስከ መስከረም 30 2017 የሚቆይ ልዩ የውጭ ምንዛሬ ተመን ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፥ ባንኩ አንድ ዶላር በ115.0121 ብር ገዝቶ በ119 ብር እንደሚሸጥ አስታውቋል።
ኦሮሚያ ባንክ ባንክ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ106.1742 ብር እየተገዛ በ119.9768ብር እየተሸጠ መሆኑን ባወጣው እለታዊ የምንዛሬ ተመን አስታውቋል።
ብርሃን ብንክ ዛሬ ባወጣው እለታዊ የምንዛሬ ዋጋው ላይ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ108.0769 ብር እየተገዛ በ119.9654 ብር እየተሸጠ መሆኑን ገልጿል።