አውሮፓ ህብረት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ሊመጡ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳለው ተገለጸ
አሜሪካ በበኩሏ በምርጫ ቅስቀሳዎች ወቅት የተገለጹ ሁሉ ስለማይተገበሩ ስጋት አይግባችሁ ብላለች
ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን በያዙበት ዕለት የዩክሬን ሩሲያ ጦርነትን እንደሚያስቆሙ መናገራቸው ይታወሳል
አውሮፓ ህብረት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ሊመጡ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳለው ተገለጸ።
የአሜሪካ ምርጫ በቀጣዩ ህዳር ወር ላይ የሚካሄድ ሲሆን እጩ ፕሬዝዳንቶች ከወዲሁ የፓርቲዎቻቸው ተወካዮች ሆነው ለመቅረብ ጫፍ ላይ ደርሰዋል።
በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዲሞክራት ፓርቲን ወክለው እንደሚወዳደሩ አስቀድመው ያሳወቁ ሲሆን የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን እያደረጉ ናቸው።
ሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው እጩ ፕሬዝዳንት ለመሆን የመጨረሻው ደረጃ ላይ ያሉት ዶናልድ ትራምፕ ቅድሚያ ለአሜሪካ በሚል አቋማቸው ይታወቃሉ።
ይህን ተከትሎም የአውሮፓ ህብረት በዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ የመጨረሻ እጩ እንደሚሆኑ የሚገመቱት ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ግምቱን ሰጥቷል።
ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን የሚያሸንፉ ከሆነም ህብረቱ ከአሜሪካ ጋር የጀመራቸው የዩክሬን ድጋፍ፣ የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶ እና ሌሎች ትብብሮች ላይ እንቅፋት ሊገጥማቸው እንደሚችል ህብረቱ ስጋት እንዳለው ከዚህ በፊት ገልጿል።
የቤልጂየም ጠቅሶ ሚንስትር አሌክሳንደር ደ ክሮ የዶናልድ ትራምፕ ወደ ፕሬዝዳንትነት መመለስ አውሮፓ በራሱ እንዲቆም ያደርገዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በኔቶ የአሜሪካ ተወካይ አምባሳደር ጁሊያን ስሚዝ በበኩላቸው እጩዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የሚሏቸውን ሁሉ እንደማይተገብሩ ተናግረዋል።
የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የደህንነት አማካሪ ጆን ቦልተን በበኩላቸው "ትራምፕ ዳግም ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ አሜሪካ ከኔቶ ትወጣለች" ማለታቸውን ዩሮ ኒውስ ዘግበዋል።