ሃውቲዎች የአሜሪካ እና ብሪታንያ ዜጎች በ30 ቀናት ውስጥ ከየመን እንዲወጡ አሳሰቡ
ቡድኑ በየመን የሚገኙ የውጭ ድርጅቶች የሁለቱን ሀገራት ዜጎች እንዳይቀጥሩ የሚያሳስብ ደብዳቤም ልኳል
አሜሪካና ብሪታንያ በሃውቲ ታጣቂዎች ይዞታዎች ላይ ከስምንት በላይ የአየር ድብደባዎችን ፈጽመዋል
የየመኑ ታጣቂ ቡድን ሃውቲ የአሜሪካ እና ብሪታንያ ዜጎች ከየመን እንዲወጡ አሳሰበ።
በመንግስታቱ ድርጅት ተቋማት እና በሰንአ በሚገኙ አለማቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶች ተቀጥረው የሚሰሩ የሁለቱ ሀገራት ዜጎች በ30 ቀናት ውስጥ ከሀገሪቱ እንዲወጡ ማዘዙንም ሬውተርስ ዘግቧል።
ቡድኑ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው አሜሪካ እና ብሪታንያ በየመን እየፈጸሙት የሚገኙት የአይር ድብደባ እየጨመረ መሄዱን ተከትሎ ነው።
አሜሪካ ባለፈው ሳምንት የየመኑን ታጣቂ ቡድን በድጋሚ የአለማቀፍ ሽብርተኛ ዝርዝሯ ውስጥ ማካተቷም የሀገሪቱን ዜጎች የማባረር ውሳኔ ላይ እንዲደርስ እንዳደረገው ተገልጿል።
እስራኤል በጋዛ ላይ የምትፈጽመውን ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ ካላቆመች የቀይ ባህር ጥቃቴን አላቆምም ያለው የሃውቲ ታጣቂ ቡድን ከህዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ ከ27 በላይ የመርከብ ጥቃት ሙከራዎችን አድርጓል።
አሜሪካና ብሪታንያም በየመን የቡድኑን ይዞታዎች ከስምንት ጊዜ በላይ በአውሮፕላን እየተመላለሱ መደብደባቸውን የሬውተርስ ዘገባ አስታውሷል።
የሃውቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ ድጋፎች አስተባባሪ ተወካዩ ፒተር ሃውኪንስ በላከው ደብዳቤ፥ የውጭ ድርጅቶች በየመን የአሜሪካ እና ብሪታንያ ዜጎችን እንዳይቀጥሩ አሳስቧል።
የሃውቲዎች ዋና ተደራዳሪ ሞሀመድ አብዱሳላም የደብዳቤውን ትክክለኛነት ያረጋገጠ ሲሆን፥ በየመን የሚገኘው የተመድ የሰብአዊ ድጋፎች ማስተባበሪያ ቢሮ ግን ማረጋገጫ አልሰጠም።
አሜሪካ እና ብሪታንያም በቀጥታ ዜጎቻቸውን እንዲያስወጡ በቀጥታ ደብዳቤ እንዳልደረሳቸው ነው ያስታወቁት።
21 ነጥብ 6 ሚሊየን ሰዎች (67 በመቶ ህዝብ) ሰብአዊ ድጋፍ ጠባቂ በሆነባት የመን የሚንቀሳቀሱ የአለማቀፍ ተቋማት ሰራተኞችን ለማስወጣት መሞከር ቀውሱን ያባብሰዋል ብሏል በየመን የብሪታንያ ተልዕኮ።