ስሜን አጥፍተዋል ያላቸውን 27 እንስቶች የ75 ሚሊየን ዶላር ካሳ የጠየቀው አሜሪካዊ
የ32 አመቱ ወጣት ከእርሱ ጋር የፍቅር ግንኙነት ነበረን ያሉ ሴቶች ፌስቡክ ላይ የሰጡት መጥፎ አስተያየት ለአዕምሮ ጭንቀት እንደዳረገው ገልጿል
የቺካጎ ነዋሪው ከ27ቱ እንስቶች ጋር የፍቅር ቀጠሮ መያዙን ባይክድም አስተያየታቸው ግን “እኔን አይገልጹም” ብሏል
በአሜሪካ ቺካጎ ነዋሪ የሆነው ወጣት በፌስቡክ ስሜን የሚያጎድፍ አስተያየት ሰጥተዋል ያላቸውን 27 ሴቶች ከሰሰ።
የ32 አመቱ ኒኮ ዲአምብሮሳዮ እንስቶቹ ላደረሱበት ጉዳት የ75 ሚሊየን ዶላር ካሳ መጠየቁም ተዘግቧል።
በኒውዮርክ በርካታ ተከታዮች ያሉትና “ለፍቅር ግንኙነት ተመሳሳይ ወንድ ቀጥረን ይሆን” የሚል ስያሜ ያለው የፌስቡክ ግሩፕ ላይ ነው ከዲአምብሮሳዮ ጋር የነበራቸውን ጊዜ ያጋሩት።
ሴቶችን ብቻ በአባልነት የያዘው የፌስቡክ ቡድን(ግሩፕ) ላይ የወጣቱን ምስል እና የነበራቸውን ቆይታ አንዲት እንስት ማጋራቷን ተከትሎም እናውቀዋለን ያሉ ሴቶች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
“መረጋጋት የራቀው፣ የፈለገውን ካገኘ በኋላ ደብዛው የማይታወቅ፣ ጉረኛ” የሚሉና ሌሎች አስተያየቶች ከዲአምብሮሳዮ ጋር የፍቅር ቀጠሮ ነበረን ካሉ ሴቶች ተሰጥተዋል።
“ከእርሱ (ዲአምብሮሳዮ) ጋር ከአንድ አመት በፊት ተገናኝተን ነበር፤ የሚያወራው ሁሉ እኔ መስማት የምፈልገውን ብቻ ነው፤ አንድ ቀን አብረን ካደርን በኋላ ግን ደብዛው ጠፋ” ብላለች አንድ እንስት።
ወጣቱ ከእንስቶቹ ጋር የፍቅር ቀጠሮ እንደነበረው ባይክድም የተሰጡት አስተያየቶች እኔን የማይገልጹና ስብዕናዬንም የሚጎዱ ናቸው ብሏል።
ኒኮ ዲአምብሮሳዮ በርካታ ተከታዮች ባሉት የፌስቡክ ገጽ ላይ ምስሉ መጋራቱና መጥፎ አስተያየቶች በመጋራታቸው ምክንያት ለአዕምሮ መታወክ፣ ለድብርትና ፍርሃት መጋለጡን ገልጿል።
ጠበቃውም በፌስቡክ ገጹ ላይ የተሰጡት አስተያየቶች የዲአምብሮሳዮን ስም የሚያጎድፉ ናቸው፤ ምስሉንም ያለፈቃዱ መጠቀማቸው ግላዊ ነጻነቱን ይጻረራል ባይ ነው።
በሰለጠነ ማህበረሰብ ውስጥ በዚህ መልኩ የግለሰብ ስብዕናን የሚጉዱ መጥፎ አስተያየቶች እንዲሰራጩ የፈቀደው የፌስቡክ ግሩፕም ሆነ እንስቶቹ ላደረሱበት ጉዳትም 75 ሚሊየን ዶላር ካሳ እንዲከፍሉ የሚጠይቅ ክስ መመስረቱን ጠበቃው መናገሩን አስገራሚ ዜናዎችን የሚያጋራው ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።