ትዊትር በትክክለኛው ሰው እጅ ላይ ወድቋል ሲሉ ዶናልድ ትራምኘ ተናገሩ
የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ ኤለን መስክ የትዊተርን የ44 ቢሊዮን ዶላር ግዢ አጠናቀዋል
ከትዊትር ታግደው የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ትዊተርን እንደማይጠቀሙ ገልጸዋል
ትዊትር በትክክለኛው ሰው እጅ ላይ መውደቁን የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ተናገሩ፡፡
አሜሪካንን ከፈረንጆቹ 2016 እስከ 2022 ድረስ 45ኛው ፕሬዝዳንት በመሆን ያገለገሉት ዶናልድ ትራምፕ ትዊተር ወደ ትክክለኛው ሰው መዛወሩን ተናግረዋል፡፡
የዓለማችን የኤሌክትሮኒክስ ተሸከርካሪዎችን አምራች የሆነው ቴስላ ኩባንያ እና ስታርሊንክ የተሰኘው የኮሙንኬሽን ሳተላይት ባለቤት ኤለን መስክ ትዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር ገዝተዋል፡፡
ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር ላይ በዓለማችን ካሉ ዋነኛ የማህበራዊ ትስስር ገጾች መካከል አንዱ የሆነው ትዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት ቢስማሙም የግዢ ስምምነቱ ሳይተገበር ቆይቷል፡፡
ኤለን መስክ በዛሬው ዕለት ትዊተር ኩባያን የተረከበ ሲሆን ቁልፍ የኩባያው አመራሮችን በማሰናበት ስራ የጀመሩ ሲሆን በቀጣይ አዳዲስ ውሳኔዎችን እንደሚወስኑ ይጠበቃል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለም የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ በፊት የነበሩ የትዊተር አመራሮች ሀሳቤን በነጻነት እንዳልገልጽ ገድቦኛል ያሉ ሲሆን አሁን ግን ኩባያው በትክክለኛው ሰው እጅ ላይ መውደቁን ተናግረዋል፡፡
ይሁንና ትዊተር ኩባንያ በኤለን መስክ መገዛቱን ተከትሎ ወደ ትዊትር ሊመለሱ ይችላሉ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በፍጹም አልመለስም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የቤት ልማት እና ሆቴል ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩት ዶናልድ ትራምፕ በ2020 የተካሄደው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤትን በሀይል ለመቀልበስ ተንቀሳቅሰዋል በሚል ከሁሉም የማህበራዊ ትስስር ገጾች መታገዳቸው ይታወሳል፡፡
ይሄን ተከትሎም ዶናልድ ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል የተሰኘ የማህበራዊ ትስስር ገጽ የከፈቱ ሲሆን ኩባንያቸው በፍጥነት ብዙ ተጠቃሚዎችን በማፍራት ላይ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በፈረንጆቹ 2021 ላይ በወጣው የፎርብስ 400 የአሜሪካ ቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ ያልተካተቱ ሲሆን በያዝነው ዓመት ግን 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ሀብት በመያዝ ከአሜሪካ 400 ባለጸጋዎች ዝርዝር ውስጥ በ343ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡