የዓለማችን ባለጸጋ ኤለን መስክ ትዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት መስማማቱ ይታወሳል
ቁጥር አንዱ የዓለማችን ቱጃር ኤለን መስክ ትዊተር ኩባንያን ለመግዛት ያሰረውን የውል ስምምነት አቋረጠ፡፡
አሜሪካዊው ቱጃር መስክ ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር ላይ ትዊተር የተሰኘውን የማህበራዊ ትስስር ኩባንያ በ44 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት ተስማምቶ ነበር፡፡
ከስምምነቱ በኋላም የትዊተር ኩባንያ ባለቤቶች ለኤለን መስክ ከማስረከባቸው በፊት የሀሰተኛ አካውንቶችን ብዛት ለማሳወቅ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም ኩባንያው ይሄንን እንዳልፈጸመ መስክ ተናግሯል፡፡
በዚህም ምክንያት ኤለን መስክ ትዊተር ኩባንያን ለመግዛት ያደረገውን ስምምነት ሊሰርዝ እንደሚችል ተናግሯል፡፡
የትዊትር ኩባንያ ሊቀመንበር በሬት ታይለር ከኤለን መስክ ጋር የገቧቸውን ስምምነቶች ለመተግበር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው ሂደቱ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችልም በግል የትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
ትዊተር ኩባንያ እና ኤለን መስክ በፈጸሙት የግዢ ስምምነትን ያፈረሰ አካል አንድ ቢሊን ዶላር የመክፈል ግዴታ እንዳለበት ይጠቅሳል፡፡
ኤለን መስክ ከትዊተር ኩባንያ በአጠቃላይ ምን ያህል ሀሰተኛ አካውንቶች እንዳሉ የማወቅ ፍላጎት ያለቸው ሲሆን ኩባንያው ይሄንን አላሳወቀኝም በሚል የግዢ ሂደቱ ለጊዜው እንዲቆም አድርገዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ትዊተር ኩባንያ ለኤለን መስክ ጥያቄ በቀጥታ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ሌሎች ምክንያቶችን እየደረደረ ነው የሚሉት ባለሃብቱ ኤለን መስክ ግዢውን ከመፈጸማቸው በፊት በዚህ ጉዳይ እርግጠኛ መሆን እንደሚፈልጉም ተናግረዋል፡፡
ትዊተር ኩባንያ በበኩሉ በየዕለቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሀሰተኛ እና አሳሳች ገጾችን በማጥፋት ላይ መሆኑን አሳውቋል፡፡
ትዊተር የሀሰተኛ ገጾች ብዛት ኩባንያው ካሉት ደንበኞች ውስጥ 5 በመቶ ብቻ ናቸው ቢልም ኤለን መስክ ግን የሐሰተኛ ገጾች ብዛት ከትዊተር አጠቃላይ ደንበኞች ውስጥ ከ20 በመቶ በላይ እንደሚሆኑ ግምቱን አስቀምጧል፡፡
የትዊተር መግለጫን ተከትሎም የኩባንያው የአክስዮን ዋጋ በ7 በመቶ ቅናሽ ያሳየ ሲሆን ኤለን መስክ መረጃው በግልጽ ካልተነገረው የ44 ቢሊዮን ዶላር ግዢ ስምምነቱን ማቋረጥ እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡
ሆኖም ኩባንያው መስክ በስምምነቱ መሰረት ቃሉን የማይጠብቅ ከሆነ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እወስደዋለሁ ብሏል፡፡