ለአሜሪካ "የማይለወጥ" ዲፕሎማሲ መፍትሄው የኒዩክሌር አቅማችን ማጠናከር ብቻ ነው - ኪም ጆንግ ኡን
የሰሜን ኮሪያው መሪ አሜሪካን መምታት የሚችሉ አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤሎች ለእይታ የቀረቡበትን አውደርዕይ ተመልክተዋል
ዶናልድ ትራምፕ በ2018 እኛ 2019 ከሰሜን ኮሪያው መሪ ጋር ሶስት ጊዜ መገናኘታቸው ይታወሳል
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ለውጭ የደህንነት ስጋታችን ብቸኛው መፍትሄ የኒዩክሌር ፕሮግራማችን ማጠናከር ነው አሉ።
ኪም ከአሜሪካ ጋር ከዚህ ቀደም የተደረጉ ድርድሮች "የዋሽንግተንን ግትርና ጸብ ፈላጊነት" ያሳዩ ናቸው ሲሉም መናገራቸውን የሀገሪቱ ብሄራው ቴሌቪዥን ኬሲኤንኤ ዘግቧል።
ሰሜን ኮሪያ አሜሪካን መምታት የሚችሉ አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን ጨምሮ ድሮኖችና የአየር መቃወሚያዎችን ለእይታ ያቀረበችበትን አውደርዕይ የጎበኙት ኪም ጆንግ ኡን የሀገራቸው ጦር ለውጭ የደህንነት ስጋቶች ዝግጁነቷን እንዲያጠናክር አሳስበዋል።
ኪም ባለፈው ሳምንት ከወታደራዊ መሪዎች ጋር ሲመክሩም የፒዮንግያንግ ወታደራዊ የኒዩክሌር ፕሮግራም "ያለገደብ" እንደሚስፋፋ መናገራቸውን አሶሼትር ፕረስ አስታውሷል።
የሰሜን ኮሪያው መሪ 47ኛ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ ስለተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ እስካሁን በቀጥታ አስተያየት አልሰጡም።
ትራምፕ በ2018 እና 2019 ከኪም ጋር ሶስት ጊዜ ተገናኝተዋል፤ በሁለቱ ኮሪያዎች ድንበር የሀገራቱን መሪዎች በማጨባበጥ ታሪካዊ ስራን ከውነዋል።
ይሁን እንጂ በሰሜን ኮሪያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች ተነስተው የኒዩክሌር ፕሮግራሟን እንድታቆም የተደረጉ ድርድሮች ውጤታማ ሳይሆኑ የኮሪያ ልሳነ ምድርም ወደ ውጥረት ተመልሷል።
ኪም በወታደራዊ አውደርዕዩ ላይ ባደረጉት ንግግር ትራምፕን በስም ባይጠቅሱም ከአሜሪካ ጋር የተደረጉት ድርድሮች ያልተሳኩበትን ምክንያት አብራርተዋል።
"ከአሜሪካ ጋር ለመደራደር እስከቻልነው ድረስ ጥረት አድርገናል፤ ይሁን እንጂ ድርድሩ ሃያላኑ ተከባብሮ መኖርን እንደማይመርጡ አሳየን፤ ሁሌም በሀይል የማሸነፍ ፍላጎታቸው የማይቀየር ፖሊሲያቸው መሆኑንም አረጋገጥን" ነው ያሉት።
አሜሪካ ከደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ጋር የምታደርገውን ወታደራዊ ልምምድ አጠናክራ መቀጠሏንም እንደ ወረራ ዝግጅት እንደሚመለከቱትና ለሀገራቱ የተቀናጀ ዝግጅት "ጠንካራ ምላሽ ለመስጠት ዝግጅታችን በብዙ እጥፍ መጨመር አለበት" ሲሉ ማሳሰባቸውንም ኬሲኤንኤ ዘግቧል።
የሰሜን ኮሪያው መሪ ከቅርብ ወራት ወዲህ የኒዩክሌር ዛቻቸውን ያጠናከሩት በጥር ወር ወደ ዋይትሃውስ የሚዘልቁት ዶናልድ ትራምፕ በፒዮንግያንግ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን እንዲያላሉ ጫና ለማሳደር ነው ተብሏል።
ከ28 ሺህ 500 በላይ የአሜሪካ ወታደሮች የሚገኙባት ደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል በበኩላቸው ከትራምፕ ጋር ጥሩ ወዳጅነት ለመፍጠር የጎልፍ ልምምድ መጀመራቸው መገለጹ የሚታወስ ነው።