ትራምፕ ማርኮ ሩቢዮን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አድርገው ሾሙ
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ማርክ ሩብዮ “ተቀናቃኞቻችንን ያለፍርሀት የሚፋለም ሰው ነው” ሲሉ አሞካሽተዋል
ሩቢዮ "ቅድሚያ ለአሜሪካ" በሚለው የትራምፕ መርህ እንዲሁም ከቻይና ጋር በተያያዘ የሚንጸባርቁት አቋም ለስፍራው እንዳሳጫቸው ተነግሯል
ትራምፕ የፍሎሪዳውን ሪፐብሊካን ሴናተር ማርኮ ሩቢዮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አድርገው ሾሙ።
ከቻይና ጋር በተያያዘ በሴኔቱ ጠንካራ አቋም በማንጸባረቅ የሚታወቁት ሩቢዮ ከሹመቱ በኋላ የሀገሪቱን የውጭ ፖሊሲ አጀንዳ ለማስፈጸም በየቀኑ ያለእረፍት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡
ትራምፕ በትላንትናው ዕለት ውሳኔያቸውን ባሳወቁበት መግለጫ ሩቢዮ “ለሀገራችን ጠንካራ ጠበቃ፣ ለአጋሮቻችን እውነተኛ ወዳጅ እና ለጠላቶቻችን ፈጽሞ የማይመለስ የማይፈራ ተዋጊ ነው” ሲሉ ገልፀዋቸዋል፡፡
የፍሎሪዳው ሴናተር በ2016 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሪፐብሊካንን የፕሬዚዳንትነት እጩን ለማሸነፍ በነበረው ሂደት ከትራምፕ ጋር ከፍተኛ ግጭት ውስጥ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡
ትራምፕ በ2016 ምርጫ ካሸነፉ በኋላ ታማኝ ደጋፊ እና አጋር ሆነው የዘለቁት ሩቢዮ ቅድሚያ ለአሜሪካ የሚለውን የትራምፕ አጀንዳ በጽኑ ከሚያቀነቅኑ ሪፐብሊካኖች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የ2003ቱን የኢራቅ ወረራ ከደገፉ የሴኔት አባላት መካከል አንዱ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሩቢዮ በሊቢያ አሜሪካ ጣልቃ እንድትገባ በመደገፍ ፣ የሶርያን መንግስት የሚቃወሙ ጃሃዲስት ታጣቂዎች ድጋፍ እንዲደረግላቸው ድምጽ በመሆን እና በ2018 በኢራን ላይ ከፍተኛ ማዕቀብ እንዲጣል በመደገፍ ባንጸባረቋቸው አቋሞች ይታወቃሉ፡፡
አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሹም ቀደም ባሉት ጊዜያት ለዩክሬን በሚደረገው ወታደራዊ እርዳታ ላይ ደጋፊ ሆነው ቆይተዋል፡፡
ነገር ግን ቆየት ብለው ለኬቭ የሚደረገው በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር ድጋፍ ኪሳራ ነው ከሚለው የትራምፕ ሀሳብ ጋር በመቆም የባይደን አስተዳደር ለዩክሬን 60 ቢሊየን ዶላር እንዲሰጥ ያቀረበውን ረቂቅ በሴኔቱ ተቃውሞዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ከአንድ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ደግሞ የዩክሬን ጦርነት ወደ መጠናቀቂያው መቅረብ እንዳለበት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
ሩብዮ በቃለ መጠይቁ " ምንም እንኳን የሩሲያ ደጋፊ ባልሆንም እውነታው ግን በዩክሬን ውስጥ ያለው ጦርነት የሚያበቃበት መንገድ በድርድር እና ስምምነት ብቻ ነው" ብለዋል፡፡
ትራምፕ እና ሩቢዮ በቻይና ላይ ጠንካራ ፖሊሲዎችን የሚያንጸባርቁ ሲሆን ፤ ትራምፕ በቻይና ምርቶች ላይ የታጠለውን የታሪፍ ጭማሪ ለማስፋፋት ሲዝቱ ሩቢዮ ለቻይናው ግዙፉ የቴሌኮም ኩባንያ ሁዋዌ የሚደረገው የቴክኖሎጂ ቁሶች ሽያጭ እንዲታገድ በተደጋጋሚ በመጠይቅ ይጠቀሳሉ፡፡
ረቡዕ እለት ለከፍተኛ ቦታ የታጩት የፍሎሪዳ ሪፐብሊካን ሴናተር ብቻ አይደሉም፤ ትራምፕ ማት ጌትዝን ለጠቅላይ አቃቤ ህግነት እጩ አድርገው አቅርበዋል።
ወግ አጥባቂ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ጌትዝ የወቅቱን ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሜሪክ ጋርላንድ በትራምፕ ላይ የፍትህ ስርአቱን እንደመሳርያነት ተጠቅመዋል በሚል በተደጋጋሚ ሲወቅሱ ተደምጠዋል፡፡
በተጨማሪም በጃንዋሪ 6 በካፒቶል ሂል በነበረው አመጽ የታሰሩትን የትራምፕ ደጋፊዎች “የፖለቲካ እስረኞች” ሲሉ ጠርተዋቸዋል፡፡