ለጋሾች ለሱዳን ሰብአዊ እርዳታ የሚውል ከ 2 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገቡ
ጦርነቱ የእርዳታ ማዕከል በሆነችው የምዕራብ ዳርፉሯ ከተማ አል ፋሽር ዙሪያ እየተስፋፋ ነው
ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሰብአዊ ጥሰት መፈጸሙን አለምአቀፍ ተቋማት የገለጹ ቢሆንም ሁለቱም ተፋላሚዎች በመብት ጥሰት እጃቸው እንደሌለበት ይናገራሉ
ለጋሾች ለሱዳን ሰብአዊ እርዳታ የሚውል ከ 2 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገቡ።
የሱዳን ጦርነት የተጀመረበትን አንደኛ አመት አስመልክቶ በተዘጋጀ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ ከሁለት ቢሊዮን ዩሮ ወይም 2.13 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሰብሰቡን የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ተናገሩ።
በጦርነቱ ምክንያት በረሃብ አፋፍ ላይ ያሉትን ሚሊዮን ሱዳናውያን የመርዳት ጥረት በቀጠለው የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ግጭት እና የጋዛ እና ዩክሬን ቀውስ ለጋሾችን በመፈለጉ ዘግይቷል።
ጦርነቱ የእርዳታ ማዕከል በሆነችው እና እስካሁን በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ባልተያዘችው የመጨረሻዋ የምዕራብ ዳርፉሯ ከተማ አል ፋሽር ዙሪያ እየተስፋፋ ነው።
የእርዳታ ሰራኞች እንደሚሉት ከሆነ የሱዳኑ ጦርነት የሚገባውን ትኩረት ያላገኘ አስከፊ የሆነ ግጭት ነው።
በፓሪሱ የገቢ ማሰባሰቢያ ላይ የአውሮፓ ህብረት 350 ሚሊዮን ዩሮ ቃል የገባ ሲሆን ፈረንሳይ እና ጀርመን እና ተባባሪዎቻቸው በተከታታይ 110 ሚሊዮን ዩሮ እና 244 ሚሊዮን ዩሮ ለመስጠት ቃል ገብተዋል። አሜሪካ የ147 ሚሊዮን ዶላር እና እንግሊዝ የ110 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ድጋፍ እንደሚያርጉ ቃል መግባታቸው ተገልጿል።
ሀገሪቱን ሶስት አስርት አመታት ለሚጠጋ ጊዜ ያስተዳደሩትን የቀድሞውን ፕሬዝደንት አልበሽርን በትብብር ከስልጣን ባስወገዱት ሁለት ጀነራሎች መካከል የተጀመረው ጦርነት እንደቀጠለ ነው።
የሱዳን ጦር በሚመሩት ጀነራል አልቡርሃን እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎችን በሚመሩት ጀነራል መሀመድ ሃምዳን ደጋሎ ወይም ሄሜቴ መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት በሺዎች እንዲገደሉ እና በሚሊዮኖች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል።
ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሰብአዊ ጥሰት መፈጸሙን አለምአቀፍ ተቋማት የገለጹ ቢሆንም ሁለቱም ተፋላሚዎች በመብት ጥሰት እጃቸው እንደሌለበት ይናገራሉ።
የአሜሪካ መንግስት በሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች የጦር ወንጀል ተጽሟል የሚል ውሳኔ ላይ መድረሱን ማሳወቁ ይታወሳል።