የዩክሬን ጦር ልዩ ኃይል እንደሚባለው ሱዳን ውስጥ አለ? ምንስ እያደረገ ነው?
የዩክሬን ጦር ልዩ ኃይል ከሱዳን ጦር ጎን ሆኖ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽን እየተዋጋ ነው ተብሏል
የሱዳን ጦር “የሩሲያው ዋግነር ቡድን ከጄነራል ሀምዳን ዳጋሎ ጎን ሆኖ እየተዋጋ ነው” ሲል መክሰሱ ይታወሳል
የዩክሬን ጦር ልዩ ኃይል (ቲሙር) በሱዳን ውስጥ በጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ከሚመራው የሱዳን ጦር ጎን በመሰለፍ እየተዋጋ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች ከሰሞኑ ወጥተዋል።
ዘ ኪቭ ፖስት በያዝነው ወር ባወጣው ሪፖርቱም “ቲሙር” የተባለው ዩክሬን ልዩ ኃይል በሱዳን ጦርነት ውስጥ እየተሳተፈ መሆኑን አሳውቋል።
የዩክሬን ልዩ ኃይል በሱዳን የሚገኘው የሀገሪቱን ጦር በመደገፍ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይልን እና ድጋፍ እየሰጠው የሚገኘውን ሩሲያ ዋግነር ቅጥረኞችን ለመውጋት እንደሆነም ነው የተገነረው።
የኪየቭ ፖስት ከዩክሬን ወታደራዊ መረጃ ምንጮች የተገኘ መሆኑን ጠቅሶ በለቀቀው አንድ አጭር ቪዲዮ ላይ የዩክሬን ልዩ ኃይል በድብቅ ኦፕሬሽን ላይ የነበረ የሩሲያ ዋግነር ተዋጊ እና ሁለት አፍሪካውያንን በቁጥጥር ስር አውሎ ሲያናገር ያሳያል።
በቪዲዮው ላይ የሚታየው የሩሰያ ወታደር የዋግነር ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን አባል መሆኑን እና ከማዕከላዊ አፍሪካ ወደ ሱዳን እንደተጓዘ ሲናገርም ተሰምቷል።
ይሁን እንጂ ቪዲዮው የት እንደተቀረጸ እና የቪዲዮው ምሉ ይዘት ግን ገለልተኛ በሆነ መንገድ ሊጣራ እንዳልቻለም ነው የተገለጸው።
ሆኖመ ግን የዩክሬን ጦር በሱዳን ውስጥ እየተዋጋ እንደሆነ ለሰተሙ አሉባልታዎች ምላሽ የሚሰጥ ነው ተብሏል።
ልዩ ኃይሉ በሱዳን ጦርነት እየተሳተፈ የሚገኝበት አላማም ከዩክሬን የጦር ግንባሮች ውጪ የሩሲያ ጥቅሞችን እና ፍላጎቶችን ማጥቃት እንደሆነም ተነግሯል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ እና የሱዳን ጦር መሪ ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ባሳለፍነው መስከረም ወር ላይ በአየርላይንድ ሻኖን አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ተገናኝተው መወያየታቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ከውይይቱ በኋላ በሰጡት አስተያየትም፤ “ከሱዳን መሪ ጋር የጋራ የደህንነት ተግዳሮቶቻችንን ማለትም በሩሲያ የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግላቸው ሕገ-ወጥ ታጣቂ ቡድኖችን እንቅስቃሴ ላይ ተወያይተናል” ብለዋል።
የሱዳን ጦር እና በጄነራል ሀምዳን ዳጋሎ የሚመራው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል እያደረጉት ባለው ውጊያ ላይ “የሩሲያው ዋግነር ቡድን ከጄነራል ሀምዳን ዳጋሎ ጎን ሆኖ እየተዋጋ ነው” የሚሉ ሪፖርቶች ሲወጡ ቆይተዋል።
11 ወራትን ባስቆጠረው ጦርነት ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፤ ከ6 ሚሊየን በላይ ሱዳናውያን ሀገር ውጥ ተፋነቅለዋል።
ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ሱዳናውያን ደግሞ ጦርነቱን ሽሽት ወደ ጎረቤት ሀገራት መሰደዳቸውን ነው ሪፖርቶች የሚያመላክቱት።