በሱዳን በቀጣይ ወራት 5 ሚሊየን ሰዎች ለከባድ ረሃብ ይጋለጣሉ - ተመድ
የድርጅቱ የሰብአዊ ጉዳዮች ሃላፊ ማርቲን ግሪፍትስ አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደረግ የጠየቁበትን ደብዳቤ ለጸጥታው ምክርቤት አስገብተዋል
ኦቻ በበኩሉ በአፍሪካ ቀንድ 64 ሚሊየን ሰዎች አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚሹ ገልጿል
በሱዳን በቀጣይ ወራት 5 ሚሊየን ሰዎች ለከባድ ረሃብ ይጋለጣሉ ሲል የመንግስታቱ ድርጅት አሳሰበ።
የድርጅቱ የሰብአዊ ጉዳዮች ሃላፊ ማርቲን ግሪፍትስ ለጸጥታው ምክርቤት በጻፉት ደብዳቤ የሁለቱ ጀነራሎች ጦርነት ለረሃብ የሚያጋልጣቸው ሱዳናውያን ቁጥር እየጨመረ ነው ብለዋል።
ጦርነቱ የግብርና ስራና የንግድ እንቅስቃሴን ማወኩን የጠቆሙት ሃላፊው፥ የምግብ ዋጋ ንረትም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁመዋል።
በተለይም በምዕራብና መካከለኛው ዳርፉር ያለው የጸጥታ ሁኔታ አሳሳቢ መሆን ለረሃብ የሚጋለጡ ሰዎችን ቁጥር በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረው እንደሚገኝም ነው ግሪፍትስ በደብዳቤያቸው ያሰፈሩት።
በቻድ በኩል ለሱዳናውያን እየቀረበ ያለው ድጋፍ “ነስፍን የሚያስቀጥል” ነው ያሉት ሃላፊው፥ አለማቀፉ ማህበረሰብ ለምስራቅ አፍሪካዋ ሀገር በፍጥነት እንዲደርስም አሳስበዋል።
በሱዳን ከኦማር ሀሰን አልበሽር መነሳት በኋላ ባገረሸው ጦርነትና በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎች ምክንያት ከ25 ሚሊየን በላይ ሰዎች ድጋፍ ጠባቂ ሆነዋል።
በሀገሪቱ ከ730 ሺህ በላይ ህጻናት በከፍተኛ የምግብ እጦት ውስጥ ይገኛሉ።
በቀጣዩ ወር አንደኛ አመቱን የሚደፍነው የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ ሃይል (አርኤስኤፍ) ጦርነት ከ8 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ከቀያቸው አፈናቅሏል።
ጦርነቱ ከሀገሪቱ ህዝብ ግማሹ እርዳታ ጠባቂ በሆነባት ሀገር ሰብአዊ ድጋፎችን ማቅረብ አላስቻለም ያሉት ማርቲን ግሪፍትስ፥ የጸጥታው ምክርቤት ጦርነቶች ረሃብን ወደማስከተል ሲቃረቡ አስቸኳይ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አልበሽርን ለመጣል የተባበሩት ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን እና ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) በረመዳን ጾም ተኩስ ያቆማሉ ተብሎ ቢጠበቅም በሱዳን ጦር እምቢታ ሳይሳካ መቅረቱም የሰብአዊ ቀውሱን እያባባሰው እንደሚቀጥል ተገልጿል።
የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (ኦቻ) በበኩሉ በአፍሪካ ቀንድ 64 ሚሊየን ሰዎች አስቸኳይ ድጋፍ ጠባቂ ሆነዋል ብሏል።
በሱዳን 25 ሚሊየን፣ በኢትዮጵያ 21 ሚሊየን፣ በደቡብ ሱዳን 9 ሚሊየን፣ በሶማሊያ ደግሞ 8 ነጥብ 3 ሚሊየን ሰዎች ሰብአዊ ድጋፍ ይጠብቃሉ ያለው ኦቻ፥ በሀገራቸው ውስጥ እና ድንበር አቋርጠው የተሰደዱ ከ23 ሚሊየን በላይ ሰዎችም የአለማቀፉን ማህበረሰብ ድጋፍ እንደሚጠበቁ ገልጿል።
የዩክሬን እና የጋዛው ጦርነት በምስራቅ አፍሪካ በጦርነትና በድርቅ ለከፍተኛ ችግር የተዳረጉ ሰዎች እንዲዘነጉ ማድረጉ ተደጋግሞ ተነግሯል።